92 ዓመት በሞላው የዓለም ዋንጫ ወድድር የአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ዋንጫ አንስተው አያውቁም
ለኳታሩ 2022 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ያለፉ አገራት 27 ደርሰዋል፡፡
እስካሁን 27 ሀገራት በዚህ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ያረጋግጡ ሲሆን ሴኔጋል ፣ ሞሮኮ ፣ ጋና ፣ ካሜሩን እና ቱኒዚያ አፍሪካን ወክለው በኳታሩ የአለም ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ፡፡
ከአውሮፓ ቤልጂየም፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ክሮሺያ፣ሆላንድ፣ ሰርቢያ፣ እንግሊዝ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ፖርቹጋል፣ ፖላንድ እና ስፔን ያለፉ ሀገራት ናቸው፡፡
ከእስያ አህጉር ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው ኳታርን ጨምሮ ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በዚህ ውድድር ላይ ያለፉ ሀገራት ናቸው፡፡
ከደቡብ አሜሪካ ደግሞ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ኢኳዶር እና ኡራጓይ አስቀድመው ለኳታሩ ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ከአሜሪካ እና ካሪቢያን አህጉር ደግሞ ካናዳ አስቀድማ ለኳታሩ ዋንጫ ከ38 ዓመታት በኋላ ማለፏን ስታረጋግጥ አሜሪካ ደግሞ ቀሪ ጨዋታ እያላት በሂሳብ ስሌት ያለፈች ቢመስልም ሜክሲኮ እና ኮስታሪካ በቀጣይ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ለዚህ ውድድር ለማለፍ ከባድ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል፡፡
ቀሪ አምስት ብሄራዊ ቡድኖች በየአህጉሪቱ በሚደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አላፊ ሀገሮቹ እንደሚወሰኑ ፊፋ በድረገጹ አስታውቋል፡፡
በዓለም ዋንጫ የወንዶች እግርኳስ ላይ 32 ብሄራዊ ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን አፍሪካ በአምስት፣ አውሮፓ በ13 ደቡብ አሜሪካ በአራት ወይም በአምስት እስያ በአራት ወይም በአምስት እንዲሁም ሰሜን አሜሪካ እና ካሪቢያን ደግሞ በሶስት ወይም በአራት ብሄራዊ ቡድኖች የሚወከሉ ሲሆን ቀሪዎቹ በየአህጉሪቱ በሚደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ተጨማሪ ብሄራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ፡፡
ከ92 ዓመት በፊት ነበር የተመሰረተው እና በአራት ዓመት አንዴ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከምስረታው ጀምሮ ለ21 ጊዜ ሲካሄድ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሁለት ጊዙ ውድድሩ አልተካሄደም፡፡
እስካሁን በተካሄዱት ውድድሮች ብራዚል አምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫን በማሸነፍ ስትመራ ጀርመን እና ጣልያን አራት አራት ጊዜ ዋንጫ በመብላት ቀዳሚ ሀገራት ናቸው፡፡
የዓለም ዋንጫ አሸናፊነት ከአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ውጪ ሌሎች አህጉር ያሉ አገራ ዋንጫውነ በልተው አያውቁም፡፡