ግብጽ ከ145 ሀገራት 19ኛ ደረጃን ስትይዝ ኢትዮጵያ 52ኛ ላይ ተቀምጣለች
የአለማችን የደህንነት ስጋት በየጊዜው እየጨመረ መሄድ ሀገራት ወታደራዊ አቅማቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ አስገድዷል።
ባለፈው አመት (2024) ሀገራት ለወታደራዊ ተግባራት የያዙት የ2.34 ትሪሊየን ዶላር በጀት ከ2023ቱ በ6 ነጥብ 8 በመቶ ማደጉም የሰጡት ትኩረት ማሳያ ነው።
በየአመቱ የሀገራትን ወታደራዊ አቅም ደረጃ የሚያወጣው "ግሎባል ፋየርፓወር" የ2025 ደረጃ ይፋ አድርጓል።
የወታደሮችና ጦር መሳሪያዎች ብዛትና ጥራት፣ አመታዊ የጦር በጀት፣ የጦር መሳሪያ ልማት እና ሌሎች ከ60 በላይ መመዘኛዎችን መሰረት አድርጎ የሚወጣው የወታደራዊ አቅም ደረጃ አሜሪካን ቀዳሚ አድርጓል።
ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ ደረጃውን የምትመራው አሜሪካ 900 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ወታደራዊ በጀት ይዛለች።
በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች ሶስት አመት ለመያዝ የተቃረበችው ሩሲያ በ2025 ፈርጣማ ጦር ካላቸው ሀገራት በሁለተኝነት ተቀምጣለች።
ከአሜሪካ በሶስት እጅ ዝቅ ያለ ወታደራዊ በጀት የምትይዘው ቻይና፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ብሪታንያ የባለፈውን አመት ደረጃቸውን አስጠብቀዋል።
በ2024 11ኛ ደረጃን ይዛ የነበረችው ፈረንሳይ አራት ደረጃዎችን በማሻሻል ሰባተኛ ላይ ተቀምጣለች ያለው ግሎባል ፋየርፓወር፥ በፓሪስ ደረጃዋን የተነጠቀችው ጃፓን ስምንተኛ መሆኗን አመላክቷል።
ቱርክ እና ጣሊያን እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ፓኪስታን ከባለፈው አመት ሶስት ደረጃዎችን ዝቅ ብላ 12ኛ ሆናለች። ጀርመን ደረጃዋን ከ19ኛ ወደ 14ኛ ማሻሻል ችላለች።
እስራኤል በ2025 የአለም ሀገራት ወታደራዊ አቅም ደረጃ 15ኛ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፥ ኢራን ከባለፈው አመት አንድ ደረጃ ዝቅ ብላ እስራኤልን ትከተላለች።
ግብጽ ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም ደግሞ 19ኛ ደረጃን ስትይዝ ኢትዮጵያ ደግሞ ከአፍሪካ አምስተኛ ከአለም ደግሞ 52ኛ ላይ ተቀምጣለች።
"ግሎባል ፋየርፓወር" ድረገጽ እንዳስነበበው በወታደሮች ቁጥር ቻይና በ2.035 ሚሊየን ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች። ህንድ በ1.455 ሚሊየን፤ አሜሪካ በ1.328 ሚሊየን ይከተላሉ።
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ በወታደሮች ብዛት አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።