በአውሮፓ የጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች ቁጥር ቅናሽ አሳየ
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ስደተኞች በአውሮፓ ጥገኝነት ጠይቀዋል ተብሏል
ጀርመን፣ ስፔን እና ፈረንሳይ ዋነኛ ስደታኛ ተቀባይ ሀገራት ሆነዋል
በአውሮፓ የጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች ቁጥር ቅናሽ አሳየ።
የዓለማችን ዋነኛ የስደተኞች መዳረሻ በሆነው አውሮፓ የጥገኝነት ጠያቂ ዜጎች ቁጥር እንደቀነሰ ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ጥገኝነት ጠያቂዎች ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ በአውሮፓ የጥገኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ስደተኞች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ነው።
ይህም በ2023 የስደተኞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በ12 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል።
ጀርመን አሁንም ዋነኛ የስደተኞች ተቀባይ ሀገር ስትሆን በተጠቀሰው ዓመት 235 ሺህ ስደታኞችን ተቀብላለች።
ስፔን 165 ሺህ ስደተኞችን ስትቀበል ፈረንሳይ ደግሞ 158 ሺህ ስድተኞችን በመቀበል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሀገራት ናቸው።
ሀንጋሪ በአንድ ዓመት ውስጥ 29 ስደተኞችን ብቻ በመቀበል ትንሽ ቁጥር ስደተኞችን የተቀበለች ሁገር ተብላለች።
ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዙዌላ እና ቱርክ ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ወደ አውሮፓ በመግባት የጥገኝነት ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው ተብሏል።
የአውሮፓ ሀገራት የስደተኞች ጉዳይ ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ እያደረጉ ሲሆን ስደተኛ ጠል የፖለቲካ ፓርቲዎች የበለጠ ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል።
ይህን ተከትሎም ከዚህ በፊት ብዙ ስደተኞችን ይቀበሉ የነበሩ ሀገራት አሁን ላይ የጥገኝነት አመልካቾችን ውድቅ ከማድረግ ባለፈ ሀገራቸውን እንዲለቁ ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው።
ለአብነትም ስዊድን ሀገሯን ለሚለቁ ስደተኞች እስከ 35 ሺህ ዶላር ቦነስ እንደምትከፍል ማሳወቋ ይታወሳል።