በ3 ሺህ 500 ቀናት አለምን የዞረው ዴንማርካዊ ወደ ቤቱ ተመልሷል
የ44 አመቱ ጎልማሳ ምንም አይነት የአየር ትራንስፖርት ሳይጠቀም “203 ሀገራትን” መጎብኘቱን ገልጿል

አለም አሳሹ በጀርመን የጀመረውን ጉዞ በማልዲቭስ አጠናቆ ሲመለስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል
ዴንማርካዊው ቶር ፔደርሰን የአለም ሀገራትን በሙሉ የመጎብኝት ህልሙን አሳክቷል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2013 ጥቅምት ወር ላይ በጀርመን የጀመረውን ጉዞ በማልዲቭስ ተጠናቆ በቅርቡ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
አለምን የዞሩና በርካታ ሀገራትን የጎበኙ ሰዎች ቢኖሩም ቢያንስ አንድ ጊዜ የአውሮፕላን በረራ አድርገዋል የሚለው ፔደርሰን ያለምንም የአየር ትራንስፖርት “203 ሀገራትን ጎብኝቻለሁ” ብሏል።
ከሀገር ሀገር ሲንቀሳቀስም ሆነ በየሀገራቱ ቆይታ ሲያደርግ እንደሀገሬው አውቶብስ፣ ባቡር እና ጀልባ መጠቀሙንም ያወሳል።
በመንግስታቱ ድርጅት እውቅና የተሰጣቸው ሀገራት ቁጥር 195 ቢሆንም ነጻ ሀገር እንደሆኑ የሚያስቡና አወዛጋቢ ቦታዎችን ጨምሮ ነው ፔደርሰን 203 ሀገራትን ጎብኝቻለሁ ያለው።
የባህርና ሎጂስቲክ ሰራተኛው ፔደርሰን 3 ሺህ 500 ቀናትን የፈጀውን ጉብኝቱን አጠናቆ ወደ ዴንማርክ ሲመለስ ከመቶ በላይ ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ እና የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቹ አቀባበል አድርገውለታል።
ፔደርሰን ባለፉት 10 አመታት እያንዳንዱን የሀገራት ጉብኝቱን እና ገጠመኙን በድረ ገጹ እና ማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ሲያጋራ መቆየቱን ኤቢሲ ኒውስ አስነብቧል።
የሀገራት የጸጥታ መደፍረስ፣ ቢሮክራሲ፣ የኮሮና እና ኢቦላ ወረርሽኝ ጉዞውን ፈታኝ አድርገውበት ነበር።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በሆንግ ኮንግ ለሁለት አመት ለመቆየት የተገደደው ፔደርሰን በህይወቱ መጥፎም አስደሳች ጊዜም ማሳለፉን ይናገራል።
“በወቅቱ አለምን የማዳረስ ጉዞዬ ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ሀገራት ይቀሩ ነበር፤ ወረርሽኙ ከቻይናውያን ጋር ማህበራዊ ህይወት እንድጀምር ሁሉ አድርጎኛል፤ የተደበላለቀ ስሜት ነው የሚሰማኝ” ይላል ፔደርሰን።
ዴንማርካዊው ጎብኝ ምንም አይነት የአውሮፕላን በረራ ካለማድረጉ ባሻገር የቀን ወጪውም ከ20 የአሜሪካ ዶላር እንዳይበልጥ ወስኖ ተነስቶ ለዚያም ተገዥ ሆኗል።
“ማንኛውም ሰው እንደሚጎበኘው ሀገር ሰው የሚበላ፣ የሚጠጣ እና የሚጓዝ ከሆነ ጉዞ እንደምናስበው ከባድ አይሆንም” የሚለው ፔደርሰን፥ ለጉብኝት እቅድ እንጂ ከፍተኛ በጀት ግድ አይደለም ባይ ነው።
ከሲሪላንካ ወደ ሀገሩ ዴንማርክ ለመግባት በባቡር 33 ቀናት የወሰደበት ቶር ፔደርሰን “ጉብኝት ስታደርጉ ከሀገሬው ጋር ተመሳሰሉ፤ ብዙ ለመማር ሞክሩ” የሚል ምክሩንም ለግሷል።