ህንድ ጎረቤቷ ቻይና የምታመርታቸው የድሮን ግብአቶች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ አገደች
ኒው ደልሂ የወታደራዊ ድሮን ግብአቶቹ የደህንነት ስጋት አላቸው ብላለች
ኒዩክሌር የታጠቁት ህንድ እና ቻይና ግንኙነታቸው በጥርጣሬ የተሞላ እንደሆነ ይነገራል
የህንድ ወታደራዊ ድሮን አምራች ኩባንያዎች የቻይናን ግብአቶች እንዳይጠቀሙ መከልከላቸው ተነገረ።
ሬውተርስ አራት የወታደራዊ ድሮን አምራች ኩባንያዎች ነገሩኝ ብሎ እንዳስነበበው፥ ኒውደልሂ የቻይና ድሮን ግብአቶች የደህንነት ስጋት አለባቸው በሚል እገዳ ጥላለች።
የወታደራዊ ድርኖቹ ካሜራዎች፣ የሬዲዮ እና ኮሙዩኒኬሽን መሳሪያዎች እንዲሁም ሶፍትዌሮቹ በቤጂንግ ለስለላ ሊውሉ እንደሚችሉ በማመን ህንድ ክልከላውን ማሳለፏ ተገልጿል።
ስማቸው ሳይጠቀስ መረጃውን ያጋሩት የኩባንያዎቹ የስራ ሃላፊዎች በምንም መንገድ ለመገናኛ ብዙሃን እንዳይወጣ እንደተነገራቸውና ጉዳዩ ሚስጢራዊ መሆኑንም አብራርተዋል።
የህንድ መከላከያ ሚኒስቴርም ለሬውተርስ ምላሽ ከመስጠት መቆጠቡን ዘገባው አያይዞ አስፍሯል።
ህንድ ከ2020 ጀምሮ ቻይና ሰራሽ ወታደራዊ ድሮኖችን ማስገባት ማቆሟን የሚያሳዩ ሰነዶች መመልከቱንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የህንን ድንበር ከሚጋሩ ጎረቤት ሀገራት ድሮኖችን መግዛት ጉልህ የደህንነት ስጋት እንደሚፈጥር ታምኖበታል።
ይህ ስጋት ቢኖርም የኒው ደልሂ የመከላከያ ኢንዱስትሪ በጎረቤቷ ቻይና ላይ ጥገኛ መሆኑን አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የሀገሪቱ የመከላከያ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ከቻይና ጋር በተደጋጋሚ የድንበር ግጭት ውስጥ የምትገባው ህንድ በ2023 የመከላከያ አቅሟን ለማሳደግ 19 ቢሊየን ዶላር መድባለች።
በተለይ በሀገር ውስጥ ድሮኖችን ለማምረት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው የሚለው የሬውተርስ ዘገባ፥ የቻይና የድሮን ግብአቶች እንዳይገቡ መከልከሉ ከፍተኛ ወጪ እያስከተለባት መሆኑን ያነሳል።
ሁለቱ ኒዩክሌር የታጠቁ ሀገራት በጥርጣሬ የተሞላው ግንኙነታቸው በድሮን ቴክኖሎጂ ላይ አለመተማመን ፈጥሮባቸዋል።
አሜሪካም በ2019 የቻይና ድሮኖች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ ማገዷ የሚታወስ ነው።
ቤጂንግ ግን ከዋሽንግተንም ሆነ ኒው ደልሂ በድሮኖቹ ላይ የሚቀርቡ የሳይበር ጥቃትና ሌሎች የደህንነት ስጋቶችን በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጓ አይዘነጋም።