ከአስተናጋጆቹ አህጉራት መካከል አፍሪካ እንደምትገኝበትም ፊፋ አረጋግጧል
የ2030 የዓለም ዋንጫ በሶስት አህጉራት ውስጥ በሚገኙ ስድስት ሀገራት እንደሚካሄድ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) አረጋገጠ።
የዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት አህጉሮች ማለትም በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ሀገራት ይካሄዳል ተብሏል።
በዚህም መሰረት የአለም ዋንጫው 100ኛ አመቱን የሚደፍንበትን የ2030 ዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታዎች አርጀንቲና ፣ ዩራጋይ እና ፓራጓይ ውስጥ እንደሚደረግ ቢቢሲ ዘግቧል።
ከመክፈቻ ጨዋታዎች በመቀጠል የሚደረጉ ሁሉም የውድድሩ ቀሪ ጨዋታዎች የውድድሩ ዋና አዘጋጅ በሆኑት በአፍሪካዊቷ ሞሮኮ፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ውስጥ እንደሚደረጉ ታውቋል።
የመክፈቻ ጨዋታዎች አርጀንቲና ፣ ዩራጋይ እና ፓራጓይ ውስጥ የሚካሄዱት የውድድሩን አንድ መቶኛ ዓመት ለማክበር በማሰብ እንደሆነም ተመላክቷል።
የአለም ዋንጫ ውድድር በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት አህጉር የሚደረግ ሲሆን ስድስቱም አዘጋጅ ሀገራት በቀጥታ ያለማጣሪያ ለውድድሩ እንደሚያልፉ ተጠቁሟል።
ይሁን እንጂ የዓለም ዋንጫ በሶስት አህጉራት ውስጥ በሚገኙ ስድስት ሀገራት የማዘጋጀት ሀሳቡ በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው የፊፋ ጉባዔ ላይ መጽደቅ ይጠበቅበታል ተብሏል።
ፊፋ በማከልም ለ2034 የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅነት ለእሲያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና ከኦሽኖያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የቀረበለትን ጥያቄ እንደሚያጤንም አስታውቋል።
የፊፋን ውሳኔ ተከትሎም የሳውዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ 2034ቱን አለም ዋንጫ ውድድር ለማዘጋጀት ለአወዳዳሪው አካል ፊፋ ጥያቄ ማቅረቡን ይፋ አድርጓል።
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ሲያቀርብ የሳውዲ አረቢያው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ሙሉ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።