ማሻሻያው 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝብ የሚኖርባት አፍሪካ ስታነሳው የቆየችውን የፍትሃዊነት ጥያቄ የመለሰ ነው ተብሏል
አሜሪካ፣ ካናዳና ሜክሲኮ በጥምረት የሚያዘጋጁት የአለም ዋንጫ 48 ሀገራት የሚሳተፉበት የመጀመሪያው የአለም ዋንጫ ይሆናል።
ከ100 በላይ የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስመለክተን የአለም ዋንጫ በሶስት ሀገራት አስተናጋጅነት የሚካሄድ መሆኑም ታሪካዊ ያደርገዋል።
የአለም ዋንጫ በ1930 በኡራጓይ ሲጀመር የተሳታፊዎቹ ቁጥር 13 ብቻ ነበር። ከ1934 እስከ 1978 የተሳታፊዎቹ ቁጥር 16 የነበረ ሲሆን፥ በ1982ቱ የአለም ዋንጫ ወደ 24 አድጓል። ከዚህ ማሻሻያ 16 አመታት በኋላም የተፋላሚ ሀገራቱ ቁጥር ወደ 32 ማደጉ ይታወሳል።
የአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በ2026ቱ የአለም ዋንጫ የሚሳተፉት ሀገራትን ቁጥር ወደ 48 አሳድጎታል።
ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የሚመሩት ፊፋ በአንድ ጊዜ ያደረጉት የ16 ተሳታፊ ሀገራት ጭማሬ ከዚህ በፊት ሲነሳ የቆየውን ቅሬታ የሚፈታ ነው።
በተለይ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝብና 54 ሀገራትን ያቀፈችው አፍሪካ በአምስት ሀገራት ተወክላ የአውሮፓና ላቲን አሜሪካ ሀገራት የተሰጣቸው ቦታ የተጋነነ ልዩነት ያለው መሆኑ ፊፋን ሲያስወቅሰው ቆይቷል።
በአዲሱ ማሻሻያም አፍሪካና እስያ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል። አፍሪካ በ2026ቱ የአለም ዋንጫ 9 ሀገራትን የምታሳትፍ ሲሆን እስያም አራት ተጨማሪ ሀገራትን የማሳተፍ እድል አግኝታለች።
የናይጀሪያ ብሄራዊ ቡድን የቀድሞው ኮከብ ሰንደይ ኦሊሴ "ማሻሻያው ለኛ ለአፍሪካውያን ከሰማይ የተላከ ነው" ብሏል። በአፍሪካ እግር ኳስ እንዲያድግ መሰል እድሎችን ማስፋት እንደሚገባም ያነሳል።
የፊፋ ማሻሻያ በኳታሩ የአለም ዋንጫ ያልተሳተፉትን እንደ ግብፅ፣ አልጀሪያና ናይጀሪያ ያሉ ሀገራት በድጋሚ ለማየት እድል ይፈጥራል።
የአውሮፓ ሀገራት ተሳትፎም ከ13 ወደ 16 እንዲያድግ ይደረጋል።
48ቱ የአለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት በምን ያህል ምድብ ተከፍለው ይጫወቱ? ምን ያህሉስ ጥሎ ማለፉን ይቀላቀሉ የሚለውን ፊፋ እያጠና ነው።
አስተናጋጆቹ ሀገራት የተሳታፊዎቹን ሀገራት በክላስተር በመመደብ የትራንስፖርት ችግሮችን ለመቅረፍም አስበዋል ተብሏል።