ፊፋ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ወደ 104 ከፍ ለማደረግ የሚያስችል አዲስ ፎርማት ይፋ አደረገ
በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ቡድኖች ቁጥርም ከ32 ወደ 48 ከፍ ይላል ተብሏል
አዲሱ ፎርማት በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል
ፊፋ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የሚደረጉ ጨዋታዎች ከ64 ወደ 104 ከፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ፎርማት ይፋ አደረገ፡፡
በቅርቡ በሩዋንዳ ኪጋሊ ጉባኤውን የሚያካሂደው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ይፋ ባደረገው ፎርማት መሰረት በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉት ብሄራዊ ቡድኖች ቁጥርም ከዚህ በፊት ከነበረው 32 ወደ 48 የሚል ይሆናል፡፡
የምድብ ቁጥርም እንዲሁ ከስምንት ወደ 12 ከፍ እንደሚል የፊፋ ምክር ቤት ማክሰኞ ባደረገው ስብሰባ ማጽደቁም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አዲሱ ፎርማት አሜሪካ፣ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ይደረጋልም ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም በተለምዶ ከእያንዳንዱ ምድብ ሁለቱ ምርጥ ቡድኖች ወደ መጨረሻው 16 ያልፉበት የነበረው አሰራር ተሻሽሎ በ2026 የዓለም ዋንጫ ስምንት ምርጥ ሶስተኛ ደረጃ ያላቸው ቡድኖች ወደ 32 ጥሎ ማለፍ ዙር የሚገቡ ይሆናል።
እንደ ፊፋ ከሆነ፤ የፊፋ ምክር ቤት በፊፋ የዓለም ዋንጫ 2026 የውድድር ፎርማት ላይ የቀረበውን ማሻሻያ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
"የተሻሻለው ፎርማት የመጋጨት አደጋን የሚቀንስ እና ሁሉም ቡድኖች ቢያንስ ሶስት ግጥሚያዎችን እንዲጫወቱ እና በተወዳዳሪ ቡድኖች መካከል የተመጣጠነ የእረፍት ጊዜ እንዲኖራቸው ያደርጋል" ተብሏል፡፡
ባለፈው አመት ኳታር ባዘጋጀችው የአለም ዋንጫ 32 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን 64 ጨዋታዎች የተካሄዱበትና በ29 ቀናት ውስጥ የተጠናቀቀ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ሜክሲኮ (1986) እንዲሁም አሜሪካ (1994) የዓለም ዋንጫን ሲያዘጋጁ ተሳታፊ ቡድኖች 24 ብቻ ነበሩ፡፡