“በ2030 የዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት በ43 በመቶ መቀነስ አለበት”- የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት
ዓለም በፓሪስ ጉባኤ ቃል-ኪዳኖች ካልተገበረ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዙ ከባድ እንደሚሆን ይገለጻል
አል ጃበር ፤ ዓለም ካለፈው ጉዞው በመማር "የማስተካከያ እርምት" መውሰድ ይጠበቅበታልም ብለዋል
በፈረንጆቹ 2030 “የዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት በ43 በመቶ መቀነስ አለበት” ሲሉ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የኢንደስትሪ እና የላቀ ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-28) ፕሬዝዳንት ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃበር (ዶ/ር) ተናገሩ።
ዓለም ሙቀትን እና ልቀትን ለመቀነስ ዓለም ካለፈው ጉዞው በመማር "የማስተካከያ እርምት" መውሰድ ይጠበቅበታልም ብለዋል አል-ጃበር፤ በዱባይ እየተካሄደ ባለውና የዓለም ቀጣይ እጣፈንታን የሚወስኑ የተለያዩ ምክረ-ሃሳቦች በሚንሸራሸሩበት “የዓለም መንግስት ጉባኤ” ላይ ባደረጉት ንግግር።
- አረብ ኢሚሬትስ በ2023 የምታዘጋጀውን ኮፕ-28 አርማ ይፋ አደረገች
- የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት፤ የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የምንተባበርበት ጊዜው አሁን ነው አሉ
"በ2030 ማለትም በሰባት አመታት ውስጥ የዓለም ልቀትን በ 43 በመቶ መቀነስ አለብን፡፡ለዚህም እስካሁን ድረስ ከሄድነበት መንገድ በተለየ መሰራዊ ለውጥ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ በጂኦፖለቲካል ውጥረቶች እና በኃይል ደህንነት ላይ ጫናዎች በሚጨምሩበት ጊዜ እርምጃን ማፋጠን በዛው ልክ ማፋጠን ይጠበቅብናል”ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
የኮፕ- 28 ፕሬዝዳንት ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃበር (ዶ/ር) ከተለመደው ውጭ የሆነ ሁሉን አቀፍ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
“የታዳሽ ሃይል አቅምን በሶስት እጥፍ ማሳደግ፣ ሃይድሮጂን የማምረት አቅምን ማጎልበት፣ የኒውክሌር ሃይልን ማስፋፋት እና የካርበን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ማበልጸግ” እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብር የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የ ኮፕ-28 አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ፤ ከህዳር 30 ወደ ታህሳስ 12 ቀን 2023 በዱባይ በሚዘጋጀው ጉባኤ ላይ አዎንታዊ አስተሳሰብን በመተግበር እና በጉባኤው ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደምትጫወትም አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ፤ በቅርቡ በተካሄደው የአቡ ዳቢ የዘላቂነት ሳምንት እንቅስቃሴ አካል የሆነው የአለም አቀፍ ታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር “ኮፕ- 28 ምኞቶችን ወደ ተግባራዊነት የሚለውጥ ተግባራዊ ጉባኤ ይሆናል” ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ዓለም በፓሪስ ጉባኤ ከስምምነት የደረሰባቸውን ቃል-ኪዳኖች ካልተገበረ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው አደጋ አሁን ካለበትም ጭምር የከፋ ሊሆን እንደሚችል ይገለጻል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፤ ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረው በ50 በመቶ ጨምሯል።
ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥ ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት ዋነኛ መፍተሄው የሙቀት መጠንን መቀነስ እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
ይህም የምድራችን የሙቀት መጠን “በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺዬስ መገደብ” እንደማለት መሆኑ ነው።
ርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ግን የምድራችን ሙቀት መጠን በያዝነው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ወደ 2 ድግሪ ሴልሺዬስ ከፍ ሊል እንደሚችልም ያስጠነቅቃሉ ተማራማሪዎቹ፤ አሁን ላይ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ ፓኪስታን ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ የመን እና በሌሎች ሀገራት እየታየ ያለው ድረቅና የምግብ እጥረት ለዚሁ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነ በአብነት በመጥቀስ፡፡