ፍዝ እሳተ ገሞራዎች ውስጥ ካርበን የማመቅ ውጥን
ተመራማሪዎች በእሳተ ገሞራዎች ውስጥ በካይ ጋዝን ማመቅ የአለምን ሙቀት ለመቀነስ ሌላኛው አማራጭ ነው ብለዋል
በፖርቹጋል የተደረገ ጥናትም በእሳተ ገሞራ ውስጥ እስከ 8 ጊጋቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ማመቅ እንደሚቻል አሳይቷል
ከፋብሪካዎች የሚለቀቅ በካይ ጋዝን በሁለት አይነት መንገድ ለመቆጣጠር ጥረት ይደረጋል።
በካይ ጋዙ (ካርበን ዳይ ኦክሳይድ) ወደ ከባቢ አየር ሳይወጣ አምቆ የመያዝና በምድር ውስጥ ማከማቸት (ካርበን ካፕቸር ኤንድ ስቶሬጅ) አንደኛው መንገድ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ከባቢ አየር ላይ የሚገኝ ካርበንን መምጠጥ (ካርበን ዳይኦክሳይድ ሪሙቫል) ነው።
ሁለቱም አማራጮች የአለምን የሙቀት መጠን ለመቀነስ አማራጭ መፍትሄ ተደርገው ቢቀርቡም አፈጻጸማቸው ብዙ ክፍተት የሚታይበት መሆኑን የአየር ንብረት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።
በቅርቡ በአውሮፓዊቷ ፖርቹጋል የተደረገው ጥናት ግን ካርበንን የማመቁ አማራጭ ላይ ከተሰራበት ውጤት ሊገኝ እንደሚችል አሳይቷል።
ጥናቱ በፍዝ (ዶርማንት).እሳተ ገሞራዎች ውስጥ ካርበን ዳይኦክሳይድን ማመቅና ማከማቸት ከባቢ አየርን ከበካይ ጋዝ የመታደግ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ያመላከተ ነው።
ከፖርቹጋል መዲና ሊዝበን በ100 ኪሎሜትር ላይ በሚገኘው የአይቤሪያን ልሳነምድር ውስጥ ባለ ፍዝ እሳተ ገሞራ ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 እስከ 8 ነጥብ 6 ጊጋቶን ካርበን ዳይኦክሳይድ ማከማቸት እንደሚቻል ነው ጥናቱ ያረጋገጠው።
ይህም የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ከ24 እስከ 125 አመታት ድረስ ከሚለቁት በካይ ጋዝ ጋር የሚስተካከል ነው።
በግንቦት ወር 2023 በጂዮሎጂ ጆርናል የወጣ ጥናትም በውቅያኖሶች ውስጥ በሚገኙ ፍዝ እሳተ ገሞራዎች ውስጥ ካርበንን የማከማቸትን አዋጭነት አሳይቷል።
የተጠቀሱት አማራጮች ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ቢታመንም ሁነኛው መፍትሄ ታዳሽ ሃይልን ማስፋፋት ነው ተብሏል።