ፊፋ የዓለም ዋንጫን በ2 ዓመት ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት እንዲካሄድ ወሰነ
የዓለም ዋንጫን በየሁለት ዓመት ይካሄድ የሚለውን ንድፈ ሀሳብ የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴርሽን ነው ያቀረበው
ንደፈ ሀሳቡንም 166 የፊፋ አባላት የደገፉት ሲሆን፤ 22 ደግሞ ተቃውመውታል
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ የወንዶች እና የሴቶች የዓለም ዋንጫ የሚካሄድበት ጊዜን ከ4 ዓመት ወደ 2 ዓመት ዝቅ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት እንዲካሄድ ውሳኔ አሳለፈ።
ፊፋ በትናትው እለት ባካሄደው ዓመታዊ ጉባዔው ላይ ነው የዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ የቀረበለትን ንድፈ ሀሳብ ተቀብሎ ጥናት እንዲካሄድበት ከስምምነት የደረሰው።
የዓለም ዋንጫን በየሁለት ዓመት ይካሄድ የሚለውን ንድፈ ሀሳብ የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴርሽን ያቀረበ ሲሆን፤ ንድፈ ሀሳቡም በአብዛኛው የፊፋ አባላት ድጋፍ ማግኘቱ ነው የተነገረው።
የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢኒፋንቲኖ “ግልጽ እና ጥልቅ” ነው ያሉትን ንደፈ ሀሳብም 166 የፊፋ አባላት የደገፉት ሲሆን፤ 22 ደግሞ ተቃውመውታል።
ንድፈ ሀሳቡን አስመለክቶ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢኒፋንቲኖ በሰጡት አስተያየት፤ “በዚህ ላይ ጥናት ማድረግ አለብን፤ ይህ እግር ኳስን ለማሳደግ የሚረዳ መንገድ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ አእምሯችንን ክፈት ማድረግ አለብን” ብለዋል።
“ዓለም ዋንጫን በየሁለት ዓመት ማካሄድ ከዓለም አቀፉ ካላንደር ጋር እንዴት እንደሚጣጣም እና ማጣሪያ ውድድሮች በምን መልኩ መዘጋጀት አለባቸው የሚለውን መመልከት አለብን” ብለዋል።
“የእግር ኳስ አፍቃሪያን በርከት ያሉ ጨዋታዎችን እና የዋንጫ ውድድሮችን ማየት ይፈልጋሉ፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ደግሞ ንግድ ሳይሆን ስፖርት ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
የቀድሞ የአርሰናል አሰልጣኝ እና በአሁኑ ወቀት በፊፋ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ልማት ሃላፊ አርሰን ዌንገር ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት “የዓለም ዋንጫ አና የአውሮፓ ዋንጫ በየሁለት ዓመት ሊካሄደ ይገባል” ማለታቸው ይታወሳል።
አርሰን ዌንገር “በውድድሮች መካከል ያለውን 4 ዓመታት መጠበቅ ለተጫዋቾች በጣም ረጅም ነው” ሲሉመ ነው በአስተያየታቸው ያነሱት።
የወንዶች የዓለም ዋንጫ በይፋ ከተጀመረበት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጥር ከ1930 ጀመሮ በየአራት ዓመቱ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድርም በይፋ ከተጀመረበት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጥር ከ1991 አንስቶ በ4 ዓመት አንዴ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።