“7 አመቴ ነው” የምትለው የ28 አመት ወጣት…
በ1996 የተወለደችው አሜሪካዊቷ ቻንታል ብሪላንድ እድሜዋን በተመለከተ ለሰዎች ማስረዳቱ አድካሚ እንደሆነባት ትገልጻለች

ቻንታል 10ኛ አመት ልደቷን በ2036 ወይንም በ40 አመቷ በልዩ ሁኔታ ለማክበር አቅዳለች
የልደት ቀን ማክበር ወይም አስቦ መዋል ለበርካቶች ትልቅ ትርጉም አለው።
ለራስ ብቻም ሳይሆን ለወላጆችና ጓደኞችም ልዩ ትርጉም የሚሰጥ በመሆኑ ተጠባቂ ነው።
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር በሚከተሉ ሀገራት በዛሬዋ እለት (የካቲት 29) መወለድ ግን ተናፋቂውን ቀን በየአመቱ ለማክበር አያስችልም።
በዘመን ቀመሩ መሰረት 28 ቀን ይዛ የምትቆየው የካቲት ወር በአራት አመት አንዴ 29 ቀን ይኖራታል።
ይህም በዚህች ቀን የሚወለዱ ሰዎች ልደታቸውን ለማክበር አራት አመት መጠበቅን አስገዳጅ ያደርግባቸዋል።
በ1996 የካቲት 29 የተወለደችው አሜሪካዊት ቻንታል ብሪላንድም ገና ሰባት አመቴ ነው ማለቷ ሻማ ተለኩሶ ኬክ የቆረሰችባቸውን ትክክለኛ የልደት ቀኖቿን በማሰብ ነው።
በኢሊኒዮስ አልጎንኪዩም በተባለ አካባቢ “በሊፕ አመት” ወይም በአራት አመት አንዴ በምትከሰተው የካቲት 29 የተወለደችው ቻንታል፥ “28 ደፍኛለው ግን ደግሞ ሰባት አመቴም ነው፤ ስለ እድሜዬ ሰዎችን ማስረዳቱ ግን አድካሚ ሆኖብኛል” ትላለች።
በርካታ ሰዎች ስለየካቲት 29 ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን የምትናገረው ወጣቷ በ2020 6ኛ ልደቷን ማክበሯን ታወሳለች።
በጸጉር ስራ የምትተዳደረው ቻንታል ልደትን ማክበር የተለየ ትርጉም እንዳለው ለሚረር ተናግራለች፤ የሚናፍቁትን ነገር በአራት አመት አንዴ ማክበርም አሳዛኝም ልዩ ደስታንም የሚፈጥር ነው ትላለች።
በአለማችን ከሚገኙ 8 ቢሊየን ሰዎች 5 ሚሊየኑ ዛሬ እንደ ቻንታል ሁሉ ተናፋቂውን ልደታቸውን እያከበሩ እንደሚገኙ ይገመታል።
ቻንታል ብሪላንድ በ2036 10ኛ አመት ልደቷን (በ40 አመቷ) ልጆች ወልዳ በልዩ ሁኔታ የማክበር እቅድ እንዳላት ገልጻለች።