በዩክሬን ለልደት ስጦታ ሆኖ የተበረከተው ቦምብ የሰው ህይወት ቀማ
በተበረከተላቸው የቦምብ ስጦታ በተወለዱበት እለት ህይወታቸውን ያጡት የዩክሬን ጦር አዛዥ አማካሪ ናቸው
አማካሪው ከወታደር ጓደኞቻቸው ስድስት ቦምቦች በስጦታ ተበርክቶላቸዋል ተብሏል
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ አማካሪው ሜጀር ሄናዲይ ቻስትያኮቭ በትናንትናው እለት በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸው አልፏል።
ቻስትያኮቭ የተበረከተላቸው ስጦታ በተወለዱባት እለት ይህቺን አለም እንዲሰናበቱ አድርጓል።
የ39 አመቱ ወታደራዊ አመራር በኬቭ በሚገኘው ቤታቸው ልደታቸውን ሲያከብሩ ከወታደር ጓደኞቻቸው ስድስት ቦምቦች በስጦታ መልክ ይበረከትላቸዋል።
እነዚህን ስጦታዎች ወደ ቤት በመውሰድ ከ13 አመት ልጃቸው ጋር እያወጡ ሲመለከቱም ልጃቸው የአንደኛውን ቦምብ ቀለበት ሲያንቀሳቅስ ያስተወላሉ።
የተደናገጡት ቻስትያኮቭ ቦምቡን ከልጃቸው ላይ ቀምተው ቀለበቱን በመሳባቸው አስደንጋጭ ፍንዳታ ተከስቷል ይላሉ የዩክሬን የዩክሬን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢጎር ኪይሜንኮ።
በዚህም ቻስትያኮቭ ወዲያውኑ ህይወታቸው ማለፉና የ13 አመት ታዳጊ ልጃቸው ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀችበት የካቲት 2022 ጀምሮ የዩክሬን ጦር አዛዥን በማማከር እውቅናን ያተረፉት ሜጀር ቻስትያኮቭ አሟሟት በዩክሬን መገናኛ ብዙሃን በተለያየ መልኩ ተዘግቧል።
ዩክሬንስካ ፕራቭዳ ጋዜጣ ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ቻስትያኮቭ ከጓደኞቹ ውስኪ እና በቦምብ ቅርጽ የተሰሩ ብርጭቆዎችን የያዘውን ስጦታ ሲከፍት ነው ፍንዳታው የተከሰተው።
በቂ ልምድ ያለውና የጦር መሪው አማካሪ የቦምብ ቀለበት ስቦ ህይወቱ አለፈ የሚለው አሳማኝ አይደለም የሚሉና በሰው እጅ ተገድሎ ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክቱ መረጃዎችም በመውጣት ላይ ናቸው።
የዩክሬን ጦር አዛዥ ጀነራል ቫለሪል ዛሉዥኒ በአማካሪያቸው ልደት ላይ ይገኛሉ ተብሎ በማሰብ የተጠነሰሰ የግድያ ሴራ ሳይኖር አይቀርም መባሉንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ጀነራል ቫለሪል የዩክሬን መልሶ ማጥቃት ወደ መቆሙ ተቃርቧል የሚል አስተያየት መስጠታቸው በፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ጭምር እንደተተቸ ይታወሳል።
የዩክሬን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን በአሳዛኙ ክስተት ዙሪያ የተጀመረው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሴራ ፖለቲካ ትንተና ተጠበቁ ብሏል።