ናይጄሪያ ከ14-17 አመት እድሜ ላይ የሚገኙ 29 ህጻናትን በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ተነገረ
ሀገሪቱ የሞት ፍርድን ያስተዋወቀችው በ1970 ቢሆንም ከ2016 ወዲህ በሞት የተቀጣ ሰው የለም
ህጻናቱ በቅርቡ የኑሮ ውድነት በመቃወም በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በነበራቸው ተሳትፎ በቀረበባቸው ክስ ነው የሞት ፍርድ ሊወሰንባቸው ይችላል የተባለው
ናይጄሪያ የሀገሪቱን የኑሮ ውድነት ቀውስ በመቃወም ሰልፍ ከወጡ ዜጎች መካከል ክስ የተመሰረተባቸውን ዜጎች በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ተሰምቷል፡፡
ከነዚህ መካከል በትላንትናው ዕለት ፍርድ ቤት የቀረቡት 29ኙ ህጻናት መሆናቸው የተነገረ ሲሆን በፍርድ ቤት በቀረቡብት ወቅት አራቱ በጭንቀት እራሳቸውን ስተው መውደቃቸው ተዘግቧል፡፡
በአጠቃላይ 76 ሰላማዊ ሰልፈኞች በ10 የወንጀል ክሶች የተከሰሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የሀገር ክህደት፣ ንብረት ማውደም፣ ህዝባዊ ብጥብጥ እና ጥቃት መከሰሳቸውን ኤፒ ዘግቧል፡፡
በዚህ የክስ መዝገብ ውስጥ ከተከሰሰሱ ሰዎች መካከል እድሜያቸው ከ14-17 የሚደርስ 29 ህጻናት ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የኑሮ ውድነት በፈጠረው ተጽእኖ የተነሳ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል እና ለወጣቶች የስራ እድል የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች ባለፉት ወራት ናይጄሪያ እና ኬንያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተካሄደዋል፡፡
በነሀሴ ወር በናይጄርያ የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደው ተቃውሞም 20 ሰዎች በጥይት ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል፡፡
የሞት ቅጣት በናጄርያ ከ1970 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ቢሆንም ከ2016 ወዲህ አንድም ሰው በሞት ተቀጥቶ አያውቅም፡፡
በአቡጃ የሚገኙት የግል ጠበቃ አኪንታዮ ባሎጉ የህጻናት መብት ህግ ማንኛውም ህጻን በወንጀል ክስ እንዲቀርብ እና ሞት እንዲፈረድበት አይፈቅድም ብለዋል።
በዚህም መንግስት ተከሳሾቹ ከ19 አመት በላይ መሆናቸው እስካላረጋገጠ ድረስ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ማቅረቡ ስህተት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፎቹ አዘጋጅ እና ሌሎች የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ህጻናቱም ሆነ በአዋቂ እድሜ ላይ ያሉ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች መንግስትን በመቃወማቸው ብቻ ለእስር ስለመዳረጋቸው እየተከራከሩ ነው፡፡
ናይጄሪያ ምንም እንኳን በአፍሪካ ድፍድፍ ዘይት በማምረት ቀዳሚ ብትሆንም ከዓለም ድሃ አገሮች አንዷ ሆና ቆይታለች።
ሥር የሰደደ ሙስና ፣ የመንግሥት ባለሥልጣኖቹ የተቀናጣ የአኗኗር ዘይቤ የሕዝቡን አኗኗር አያንጸባርቅም በሚልም ተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብባቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የህክምና ባለሙያዎች አነስተኛ ደመወዝን በመቃወም የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
የ210 ሚሊዮን ህዝብ ባለቤት የሆነችው ሀገር ከፍተኛ ርሀብ ከተከሰተባቸው የአህጉሪቷ ክፍሎች መካከል አንዷ ናት ፤ 28 በመቶ ላይ የሚገኝው የዋጋ ንረት ከአስርተ አመታት በኋላ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡