ናይጄሪያ እና ዲአር.ኮንጎ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አለፉ
ናይጄሪያ አንጎላን እና ዲአር.ኮንጎ ደግሞ ጊኒን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል
ዛሬ ምሽት በሚካሄደው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ማሊ ከአስተናጋጇ ኮትዲቮር እና ደቡብ አፍሪካ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ይጋጠማሉ
ናይጄሪያ እና ዲአር.ኮንጎ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አለፉ።
ትናንት ምሽት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ናይጄሪያ እና ዲአር.ኮንጎ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ናይጄሪያ አንጎላን እና ዲአር.ኮንጎ ደግሞ ጊኒን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ናይጀሪያ በአድሞላ ሉክማን አማካኝነት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ባስቆጠራት ግብ ለመምራት የሚያስችላትን ግብ ማግኘት ችላለች።
የግቧን መቆጠር ተከትሎ አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት የአንጎላ ተጨዋቾች በርካታ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ምንም ግብ ሳይቆጠርት በናይጄሪያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ግብጽን በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀለችው ዲአር.ኮንጎ ጊኒን 3-1 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተቀላቅላለች።
የኮንጎው አምበል ቻንሴል ምምባ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በጊው አጥቂ መሀመድ ባዮ ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት ጊኒ የፍጽሞ ቅጣት ምት አግኝታለች።
አጥቂው መሀመድ ባዮም ፍጹም ቅጣት ምቱን ወደ ግብ በመቀየር ጊኒ እንድትመራ አስችሏት ነበር።
ነገርግን ብዙም ሳይቆይ የዲአር.ኮንጎ አጥቂ ምምባ የአቻነት ግብ አስቆጠረ።
ከፍተኛ የሆነ ጥፋቶች በተስተዋሉበት በዚህ ጨዋታ በዲአር.ኮንጎው አጥቂ ሲላስ ላይ በተፈጸመ ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ግጣት ምት ዮአኔ ዊሳ ከመረብ በማገናኘቱ ዲአር.ኮንጎ 2-1 መምራት ቻለች።
በጨዋታው የመጨረሻ 10 ደቂቃ የጊኒ ግብ ጠባቂ መውጣቱን የተመለከተው የቀድሞው የዌስትሀም ተጨዋች አርቱር ማሱዋኩ ሶስተኛዋን ግብ አስቆጥሯል።
ዛሬ ምሽት በሚካሄደው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ማሊ ከአስተናጋጇ ኮትዲቮር እና ደቡብ አፍሪካ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ይጋጠማሉ።
ያልተጠበቁ ውጤቶችን በማስተናገድ ላይ ባለው የዋንጫ ውድድር ትልቅ ግምት የተሰጣቸው እንደ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ አልጀሪያ እና ጋና የመሳሰሉ ቡድኖች ከሩብ ፍጻሜው በፊት ተሰናብተዋል።