ናይጄሪያ 10 ዜጎቿን በሀገር ክህደት በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ተነገረ
ተከሳሾቹ ባሳለፍነው ወር በሀገሪቷ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ሀገሪቷን ለማፈራረስ ተንቀሳቅሰዋል በሚል በሀገር ክህደት ክስ ቀርቦባቸዋል
ተቃውሞውን ተከትሎ 700 ሰዎች ሲታሰሩ 23 የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ በፖሊስ ስለመገደላቸው ተሰምቷል
ናይጄሪያ 10 ዜጎቿን በሀገር ክህደት በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ተነገረ።
ናይጄሪያ ባሳለፍነው ወር በሀገሪቱ በተካሄደው የመንግስት ተቃውሞ ሰልፍ ሀገርን ለማፍረስ እና አለመረጋጋትን ለመፍጠር ሆን ብለው ተንቀሳቅሰዋል ባለቻቸው ዜጎቿ ላይ በሀገር ክህደት ክስ ከፍታለች፡፡
ባሳለፍነው ወር በናይጄርያ የሚገኝው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲሻሻል የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በመሳተፍ ከተያዙ 700 ሰዎች መካከል አስሩ በፌደራሉ ፍርድ ቤት በሀገር ክህደት ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በተቃውሞው ከጸጥታ አካላት ጋር በነበር ግጭት 7 ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ ሲያሳውቅ የመብት ተሟጋቾች በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር 23 እንደሚጠጋ ተናግረዋል፡፡
በማህበራዊ ትስስር ገጽ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ “ተርበናል” እና “በናይጄሪያ ያለው መጥፎ አስተዳደር ይብቃ” የሚሉ መፈክሮች የተንጸባረቁበት ነበር።
በሀገሪቱ የሚገኝው ወርሀዊ የዋጋ ንረት 30 በመቶ እና ከዛ በላይ ሲሆን የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀብ እንዲሁም መንግስት የሚያወጣቸው የተጋነኑ ወጪዎች የተቃውሞው ምክንያቶች ነበሩ፡፡
በትላንትናው እለት ፍርድ ቤት የቀረቡት 10 ዜጎች የህዝብ ንብረትን በማውደም ፣ የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት በማድረስ እና ከብሪተንያ ዜጎች ጋር በመመሳጠር የናጄርያን መንግስት መከላከያ ሀይሉ እንዲቆጣጠረው ጥሪ በማድረግ ነው ክስ የቀረበባቻው፡፡
ለአንድ ወር ያህል በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎቹ በትላንትናው እለት የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎ ለፖሊስ የ8 ቀናት ተጨማሪ የግዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ቀሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታሳሪዎች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነገር ባይኖርም ከአስሩ ተጠርጣሪዎች ጋር አሲሯል የተባለው የብሪታንያ ዜጋ በፖሊስ እየታደነ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የክስ ሂደቱ በበርካታ ናጄሪያውያን ዘንድ ተቃውሞ ሲገጥመው የፕሬዝደንት ቦላ ቲኒቡ መንግሰት ተቃውሞን ለማፈን የሚሄድበትን ርቀት አመላካች ነው በሚል ተተችቷል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽል በበኩሉ የፍርድ ሂደቱን የዜጎችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጋፋ “አሳፋሪ” የፍርድ ሂደት ሲል ገልጾታል፡፡
በወጣት እና በጎልማሳነት እድሜ ላይ የሚገኙት በሀገር ክህደት ክስ የተከሰሱት 10 ናይጄርያውያን በፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ተብለው ከተገኙ የሞት ፍርድ ሊፈረድባቸው እንደሚችል ኤፒ ዘግቧል፡፡