የአየር ንብረት ለውጥ ከ4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ማድረሱ ተገለጸ
ባለፈው በግማሽ ክፍለ ዘመን ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል
በዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ህይወታቸውን ከሚያጡ 10 ሰዎች ውስጥ ዘጠኙ በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ናቸው ተብሏል
የአየር ንብረት ለውጥ ከ4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ማድረሱ ተገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፉት 50 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ያደረሳቸውን ጉዳቶች አስመልክቶ ያስጠናውን ጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
በዚህ ሪፖርት መሰረትም ከፈረንጆቹ 1970 እስከ 2021 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ12 ሺህ በላይ አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተከስቷል።
- የአየር ንብረት ለውጥ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ በ10 ሚሊየን ሰዎችን ሊያፈናቅል ይችላል- የዓለም ባንክ
- የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት፤ የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የምንተባበርበት ጊዜው አሁን ነው አሉ
በነዚህ አደጋዎች ምክንያትም ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር ሁለት ሚሊዮን ሲደርስ 4 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል።
በዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዐለማችን ከሚሞቱ 10 ሰዎች መካከል ዘጠኙ በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች መሆናቸውንም ተመድ አስታውቋል።
አስከፊ ድርቅ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ ፣የአውሎ ነፋስ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የደረሱ የአየር ንብረት አደጋዎች ናቸው።
በአፍሪካ ብቻ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ 1 ሺህ 800 አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተከስቶው 755 ሺህ ህዝብ ሲሞት ከ185 ቢሊዮን በላይ ዶላር ደግሞ የኢኮኖሚ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል።
አሜሪካ ብቻዋን በዚሁ የአየር ንንበት ለውጥ ምክንያት የ1 ነጥብ 7 ትሪሊዮን የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሶባታል ተብሏል።
እስያ አህጉር ከሁሉም አህጉራት በበለጠ በአየር ንብረት ለውጥ የተጠቃ ሲሆን በነዚህ አደጋዎች ምክንያት የ1 ነጥብ 4 ትሪሊን ዶላር ጉዳት አድርሷል።