የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት፤ የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የምንተባበርበት ጊዜው አሁን ነው አሉ
አረብ ኢሚሩትስ በታዳሽ ኃይል ላይ ኢንቨስት በማድረግ በአረቡ ዓለም ፈር ቀዳጅ ሀገር መሆኗ ይታወቃል
ሱልጣን አል ጃበር ፤ "ኮፕ-28" ዓለም ለአየር ንብረት ፋይናንስ አዳዲስ ዝግጅቶችን የሚያደርግበት ይሆናል ብለዋል
ከቀናት በፊት የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት ሆነው የተሸሙት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሱልጣን አል ጃበር (ዶ/ር) “የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የምንተባበርበት ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ሱልጣን አል ጃበር ይህን ያሉት በአቡ ዳቢ እየተካሄደ ባለው የዓለም መጻኢ የኃይል አማራጭ ጉባኤ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የምታዘጋጀው የ "ኮፕ-28" ጉባኤ በዓለም ላይ እያጋጠሙ ያሉ ጉዳዮች እና ተግዳሮቶች አስፈላጊነት ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
- በኮፕ 28 ጉባዔ በአየር ንብረት እርምጃ ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ሁሉንም አቅሞች እንጠቀማለን- ዶ/ር ሱልጣን አል ጃበር
- አረብ ኢምሬት ለታዳሽ ሀይል ልማት 50 ቢሊዮን ዶላር ማፍሰሷን ገለጸች
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እንደሌላው ዓለም በከፍተኛ የሙቀት መጠን አደጋ እየተጎዳች እንደምትገኝ የተናገሩት የጉባኤው ፕሬዝዳንት የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት ሱልጣን አል ጃበር፤ ሀገራቸው የለውጥ ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በእውነተኛ አጋርነት አስፈላጊነት ላይ ባላት ጽኑ እምነት እንዲሁም ባለፉት 50 ዓመታት ባስመዘገበችው ትልቅ እድገት ተግዳሮቶችን በመጋፈጥ እና የወደፊቱን አስቀድሞ በመመልከት ረገድ ኃላፊነቷ እንደምትወጣም አስረግጠው ተናግረዋል ሱልጣን አል ጃበር።
ሱልጣን አል ጃበር ንግግራቸው ሲቀጥሉም “የተባበሩት አረብ ኢሚሩትስ በታዳሽ ኃይል ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እና ወደፊት ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ረገድ አህጉራዊ ፈር ቀዳጅ ነበረች እና አንዳንዶች የማስዳር ኩባንያን ዓላማ ለማሳካት ያለንን አቅም ሲጠራጠሩ እኛ ግን በአቀራረባችን ቀጠልን ፤ አሁንም ቢሆን የኢነርጂ ልቀትን በመቀነስ በዘላቂነትን የሃይድሮካርቦን ስራችን ዋና አካል አድርገን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
ዓለም ዛሬ እያስመዘገበች ያለችዉ መሻሻል ቢኖርም የፕላኔቷን የሙቀት መጠን ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳይበልጥ ለማድረግ እየጣርን ስለሆነ ከራሳችን ጋር ግልጽ መሆን እና በፍጥነት መንቀሳቀስ አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ኮፕ-28 የሰሜን እና የደቡብ ሀገራት እርስ በርስ የሚደማመጡበት እንዲሁም ዓለም ለአየር ንብረት ፋይናንስ አዳዲስ ዝግጅቶችን እና ዘዴዎችን እንዲያዘጋጅ የሚያስችል ጉባኤ መሆን አለበትም ሲሉም አክለዋል፡፡
"ሁላችንን የሚጠብቀን ተግባር ትልቅ ነው፣ ዕድሉም ትልቅ ነው፣ እናም የተመጠነ ልቀት እንዲኖር በማድረግ የላቀ ስኬት እና በገበያዎች ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ይቻላልም" ነው ያሉት የኮፕ-28 ፕሬዝዳንቱ ሱልጣን አል ጃበር፡፡
ይህን ወሳኝ ወቅት ለመጋፈጥ ዓለም አንድ መሆን ይችል እንደሆነ ጥያቄዎችን ያነሱት አል-ጃብር፤ ዓለም በሚቀጥሉት ሰባት አመታት ውስጥ ልቀትን በግማሽ እንደሚቀንስና ይህን ምኞት እውን እንዲሆን በሰው ልጆች ችሎታ ላይ ትልቅ እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
መጪው ጊዜ የማይቆም በመሆኑ ሁሉም ሰው እንዲተባበር፣ ጥረቶችን እንዲቀላቀል፣ ኃሳቦችን እንዲለዋወጥ እና መርህን ወደ ተግባር በመለወጥ ተጨባጭ ተግባራዊ እድገት እንዲያመጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።