32ኛው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ስነ ስርዓትም ዛሬ ተካሂዷል
በጃፓን አስተናጋጅነት የሚካሄደው 32ኛው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።
በዛሬው እለትም በኦሎምፒክ ጨዋታዎቹ ላይ የሚሳተፉ ሀገራ ተወካዮች በተገኙበት ደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
የመክፈቻ ምርሃ ግብሩ በኪቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች የ1 ደቂቃ ፀሎት በማድረግ ነው ተጀመረው።
በኦሎምፒክ ጨዋታዎቹ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ተወካዮችም የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ እና ሌሎች ሀገራቸውን የሚያስተዋውቁ ትርኢቶችን በመክፈቻው ላይ አሳተዋል።
ኢትዮጵያ ግን በመክፈቻው ላይ በሁለት ሰዎች ብቻ በመወከል መክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ ታድማለች።
ጃፓን በቶክዮ 2020 ኦሎምፒክ መክፈቻ ስነ-ስርአት የተለያዩ ቀለም ባላቸው ርችቶች ደምቃ በመታየት ላይ ነች፡፡
በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ኦሎምፒክ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 መደረግ ቢኖርበትም በኮቪድ -19 ምክንያት ለአንድ አመት ተራዝሞ እየተካሄደ ነው።
በዘንድሮው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ከ205 ሀገራት የተውጣቱ ከ11 ሺህ በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ከስፍራው ተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ 33 አይነት ስፖርታው ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ በውድድሩ ለሚያሸንፉ አትሌቶችም 5 ሺህ ሜዳሊያዎች ለሽልማት ተዘጋጅተዋል።
ኢትዮጵያ የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ በ4 አይነት የስፖርት አይነቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ውኃ ዋናና ከቴኳንዶ ትሳተፋለች።
ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚጓዙት አትሌቶችና አሰልጣኞች 65 ሲሆኑ፤ በጥቅሉ ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ጃፓን የሚያመራው ልዑክ ከ90 በላይ አባላት የያዘ መሆኑንም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለአል ዐይን መግለጹ ይታወሳል።