ኢትዮጵያ እና ቶኪዮ ከ57 ዓመታት በኋላ ዳግም በኦሎምፒክ መድረክ
አበበ ቢቂላ በ1964 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ያስመዘገበው ድል ከ57 ዓመታት በኋላ የ ይደገም ይሆን?
በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ በቴኳንዶ ስፖርት ትሳተፋለች
የጃፓንና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከ1930 ዓ.ም የጀመረ ቢሆንም ወዳጅነታቸው የበለጠ ማስታወሻ ያገኘው ግን እ.ኤ.አ ከ 1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ መሆኑ ይገለጻል።
የኢትዮጵያና የአፍሪካ የአትሌቲክስ ጀግና ተብሎ የሚነሳው ሻምበል አበበ ቢቂላ በጣሊያን ሮም በባዶ እግሩ ማራቶንን ከማሸነፍ ባለፈም የዓለምን ክብረ ወሰን አሸሽሎ ነበር።
የአበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ማሸነፍ ነጮች፤ በጥቁር ከተሸነፉበት የአድዋ ድል በኋላ ዓለምን ያነጋገረ ትልቅ ዜና እንደነበር በታሪክ ይነሳል።
በወቅቱ የነበሩ ዘጋቢዎችም “ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብና ወታደሮች ብትመድብም ኢትዮጵያ ግን በአንድ ሰው (በአበበ ቢቂላ) መላውን ሮም ወረረች” ተብሎ መዘገቡ ይጠቀሳል።
ሻምበል አበበ ቢቂላ በአውሮፓ ያሸነፈውን ኦሊምፒክ በእስያ ጃፓንም መድገሙ ጃፓናውያንንና ኢትዮጵያውያንን በጥሩ ሁኔታ እንዳገናኛቸውና እንዳወዳጃቸው ይጠቀሳል።
አዲስ አበባና ቶኪዮ ግንኙነታቸው የሚጀምረው በ1930 ቢሆንም ቅሉ የበለጠ የወዳጅነታቸው መጠን የጨመረው ግን እ.ኤ.አ ከ1964 የሻምበል አበበ ቢቂላ አስደናቂ የማራቶን አጨራረስ በኋላ እንደሆነ ይነሳል።
በዚህም መሰረት ከ57 ዓመት የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ ኢትዮጵያ ለጃፓን፤ ጃፓንም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አክብሮትና የማይረሳ ትዝታ እንዳላቸው ይጠቀሳል።
የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ባለሥልጣናት የእርስ በእርስ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2006 የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሚስተር ኮይዙሚ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ነበር።
በ2007 ዓ.ም ደግሞ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትና ከወራት በፊት በራሳቸው ፈቃድ ከስልጣናቸው ተነሱት ሺንዙ አቤ በአዲስ አበባ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራን አሸናፊው ሻምበል አበበ ቢቂላን የሚያስታውስ ንግግር አድርገው ነበር።
ሚስተር አቤም ከንግግራቸው በኋላ፤ ከአበበ ቢቂላ ልጅ የትናየት አበበ ጋር ተገናኝተው ተገናንተው ተነጋግረው ነበር። በወቅቱ ሚስተር አቤ የ1964ን ኦሊምፒክ “ጃፓንንና ኢትዮጵያን በጥብቅ ያቆራኘና ግንኙነታቸውን ያጠናከረ ትዝታ ነው” ብለው ነበር።
ጃፓን እ.አ. አ በ 1964፤ 18ኛውን ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስታዘጋጅ ከእስያ አህጉር የመጀመሪያ ነበረች፤ መዲናዋ ቶኪዮ በኦሊምፒክ ውድደሮች በርካታ ተወዳዳሪዎችን ያስተናገደች ሲሆን፤ ጨዋታዎቹም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሳተላይት አማካይነት በቴሌቪዥን ተላልፈው እንደነበር በታክ ተጽፏል።
ጃፓንም 18ኛውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ካስተናገደቸች ከ57 ዓመታት በኋላ፤ 32 ኛውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለማዘጋጀት የወሰደችውን ኃላፊነት በ2020 እ.ኤ.አ ማጠናቀቋን ገልጻ ነበር።
ይሁንና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዙ አቤ እና የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች ከአባል ሀገራት ጋር ከተነጋሩ በኋላ ጨዋታዎቹ “ቶኪዮ ኦሊምፒክ 2020 “ የሚለውን ስም ይዞ ዘንድሮ እንዲካሄድ ተወስኗል።
የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሀገራት በአዲስ የዝግጅት መርሃ ግብር ከሰሞኑ ወደ ቶኪዮ ሲጓዙ ጃፓንም በአዲስ የኦሊምፒክ መንደርና በአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ትቀበላቸዋለች።
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለከፍተኛ የሜዳሊያ ቁጥር ውስጥ ከሚታጩ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን እ.አ.አ ከ1956 ጀምሮ በተሳትፎዋ ብቻ ሳይሆን በአሸናፊነቷም ትታወቃለች።
ከሰሞኑ በሚጀመረው 32 ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክም ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በውኃ ዋናና በቴኳንዶ እንደምትወዳደር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ በቴኳንዶ ስፖርት በአትሌት ሰለሞን ቱፋ እንደምትወከል ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽንም በቶኪዮ “2020” ለሚሳተፈውን ልዑካን ቡድን አሸኛኘት ማድረጉ ተገልጿል።