3 ነጥብ 2 በመቶ ኢትዮጵያውያን የስኳር ህመምተኞች መሆናቸውን ያውቃሉ?
የስኳር ህመምተኞች ቀን የፊታችን እሁድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ ይከበራል
9 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በቅድመ ስኳር ህመም ውስጥ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል
የስኳር ህመምተኞች ቀን የፊታችን እሁድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ ይከበራል።
የስኳር በሽታ ሰውነታችን በቂ የኢንሱሊን ንጥረ ነገር ማመንጨት ሳይችል ሲቀር ወይም በሰውነታችን ውስጥ የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ሲቀር የሚከሰት በሽታ ነው።
ባልተለመደ ሁኔታ የዉሃ ጥማት ፣ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት፣ ከባድ የረሃብ ስሜት፣ ዘላቂ የድካም ስሜት፣ የእይታ መደብዘዝ፣ ምክንያቱ ያልታወቀ ክብደት መቀነስ እና ሌሎችም የስኳር በሽታ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
በዚህ ገዳይ በሽታ ዙሪያ የሰዎችን ግንዛቤ ለመፍጠር በየዓመቱ ህዳር 5 ቀን የስኳር ህመምተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን ለ31ኛ ጊዜ የፊታችን እሁድ ይከበራል።
በዚህ በዓል አከባበር ዙሪያም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር መግለጫ ሰጥተዋል።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ህይወት ሰለሞን እንዳሉት 3 ነጥብ 2 በመቶ ኢትዮጵያዊያን የስኳር ህመምተኞች ናቸው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ባደረገው ጥናት መሰረትም ከስኳር ሁኔታ መዛባት ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 12 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን 9 ነጥብ 1 በመቶዎቹ ደግሞ በቅድመ ስኳር ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ፕሬዘዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የስኳር ህመምተኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው ዜጎች በየጊዜው ምርመራ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በተለይም በአይነት አንድ የስኳር ህመም የሚጠቁ ህጸናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው የሚሉት ዶክተር ጌታሁን የስኳር ህመም የአዋቂዎች እና የሀብታሞች በሽታ ነው የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት መታረም አለበትም ብለዋል።
እድሜ፣በዘር የሚተላለፍ የስኳር ታማሚ መኖር፣ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ከመጠን ያለፈ አልኮል መውሰድ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ተጠቂ መሆን እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት ደግሞ ለአይነት ሁለት የስኳር ህመም መንስኤዎች መሆናቸወንም ዶክተር ጌታሁን ተናግረዋል።
እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የአይነት ሁለት የስኳር ህመም የተስተካከለ አመጋገብን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ መከላከል እንደሚቻልም የማህበሩ ፕሬዘዳንት አክለዋል።
ያልታወቀ ወይም ታውቆ በቁጥጥር ስር ያልዋለ የስኳር ህመም በአጭር ጊዜ ለከፍተኛ የስኳር መጠን መዛባት፣ ለአይን ብርሃን ማጣት፣ለጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ወይም ስትሮክ፣ ለኩላሊት መድከም፣ ለልብ ድካም እና ሌሎች ተጨማሪ በሽታዎች ስለሚያጋልጥ ሁሉም ሰው ቤጊዜው የስኳር መጠኑን እንዲለካም ዶክተር ጌታሁን አሳስበዋል።
የስኳር በሽታ በሰዎች ላይ መኖሩ ከተረጋገጠ ተገቢው ክትትል እና ህክምና ከተደረገለት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር የሚቻል ሲሆን ክትትል እና ጥንቃቄ የማይደረግ ከሆነ ግን ለከፋ ስቃይ እና ለሞት ይዳርጋል።