በኤካ ኮተቤና ሚሊኒየም አዳራሽ ያሉ የጽኑ ህክምና አልጋዎች ሙሉ ለሙሉ በህመምተኞች መያዛቸው ተገለጸ
ህጻናት እና ወጣቶችም በቫይረሱ ተይዘው ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል እየገቡ ነው ተብሏል
ኢትዮጵያ እስካሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ገደማ ዜጎቿን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሰጥታለች
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ፤ወደ ጽኑ ህክምና የሚገቡ እና ህይወታቸው የሚያልፉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዕለታዊ ሪፖርት ያስረዳል።
ዜጎች ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው የለይቶ ህክምና ከሚደረግባቸው ማዕከላት መካከል ኤካ ኮተቤ እና የሚሊኒየም ኮቪድ 19 ህክምና ማእከል ተጠቃሽ ናቸው።
አል አይን አማርኛ በነዚህ ማዕከላት የኮሮና ቫይረስ ህመምተኞች አገለግሎት ምን ይመስላል ሲል የማዕከላቱን አመራሮች ጠይቋል።
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ተጠባባቂ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ ገብረእግዚያብሄር ለአልአይን እንዳሉት ካለፉት ሶስት ሳምንታት ጀምሮ በቫይረሱ ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በቫይረሱ ተይዘው መተንፈስ ተስኗቸው ወደ ሆስፒታል የሚመጡት ሰዎች እንደ ከዚህ በፊቱ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው እና አዛውንቶች ብቻ አይደሉም የሚሉት ዶክተር ዮናስ ወጣቶች እና ህጻናትም በቫይረሱ ተይዘው ጽኑ ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በቫይረሱ ተጠቅተው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አሁን ላይ በኤካ ኮተቤ ሙሉ ለሙሉ የጽኑ ህክምና መስጫ አልጋዎች በታካሚዎች ተይዘዋል ብለዋል።
የጽኑ ህክምና መስጫ አልጋዎች ሙሉ ለሙሉ መያዛቸውን ተከትሎም በየቀኑ በአማካኝ 10 ሰዎች አልጋ አጥተው እየተጠባበቁ መሆኑንም ዶክተር ዮናስ ተናግረዋል።
በየዕለቱ ነውእየፈለጉ በቫይረሱበእድሜ የገፉህመም የገቡ ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶች ጥንቃቄ ሻ ሚሊኒየም ስርጭት በሙሉ ለሙሉ መሙ
ህብረተሰቡ አሁንም እየተዘናጋ ነው ነገር ግን እኛ ጋር በቫይረሱ ተይዘው እና ህይወታቸውን ለማትረፍ ተጨማሪ ህክምና እና መተንፈስ ተቸግረው የሚመጡ ሰዎች እየጨመረ ነው።
ቀጣዮቹ ቀናት በዓላት የሚበዙበት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ህብረተሰቡ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ብለዋል።
የሚሊኒየም ኮቪድ 19 ህክምና ማእከል ኮሚውኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ በማዕከሉ የጽኑ ህክምና አልጋዎች ሙሉ ለሙሉ በታካሚዎች መያዙን አስታውቋል።
በየዕለቱ ህክምና ፈልገው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ለማስተናገድ ህይወታቸው የሚያልፉ ወይም አገግመው ወደ ቤታቸው ከሚሄዱ ሰዎች ብቻ በሚገኙ አልጋዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ማዕከሉ ገልጿል።
ከአምስት ሳምንታት በፊት በዚህ ማእከል የነበረው የታካሚዎች ቁጥር 12 የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰአት የታካሚዎች ቁጥር ወደ 158 ማሻቀቡንም ተናግሯል።
ከ158 ታካሚዎች ውስጥ 50 የሚሆኑት በከፍተኛ ድጋፍ እና በማሽን እገዛ ላይ ያሉ ታካሚዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ታካሚዎች ደግሞ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ የኦክሲጅን ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛልም ብሏል።
ይህ ሁኔታ የማእከሉን የጽኑ ህክምና አቅም እየፈተነው ሲሆን ከተለያዩ የጤና አገልግሎት ተቋማት እንዲሁም ከማህበረሰቡ ወደ ማእከሉ ለኮቪድ ጽኑ ህክምና እየተመሩ ያሉ ታካሚዎችን ለማገልገል ከቀን ወደ ቀን እየከበደው እንደመጣም ማዕከሉ አስታውቋል።
በመሆኑም ማስክን በትክክል ማድረግ እንዲሁም የእጅ ንጽህናን በአግባቡ መጠበቅ አሁንም ቢሆን ወደር የሌላቸው መፍትሄዎች ስለሆኑ ማህበረሰቡ ሳይዘናጋ እነዚህን እርምጃዎች እንዲተገብር አሳስቧል።
በተጨማሪም እድሜያቸው ከ35 አመት በላይ የሆነ ግለሰቦች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ጣቢያዎች በመሄድ የኮቪድ 19 ክትባትን ውሰዱ ያለው ማዕከሉ ክትባቱን ከወሰዱም በኪቪድ 19 ምክንያት የሚከሰቱ መዘዞችን የማምለጥ ከለፍተኛ እድል አላቸው ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
በኢትዮጵያ እስከ ነሀሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን 4 ሺህ 606 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ለ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ገደማ ዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መስጠቷን የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ ሪፖርት ያስረዳል።