በኢትዮጵያ ጽኑ የኮሮና ታማሚዎች ቁጥር ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን የጤና ሚኒስትሯ አስታወቁ
የበሽታው የስርጭት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ባለባት በኢትዮጵያ ባለፉት 10 ቀናት ብቻ የ123 ሰዎች ህይወት አልፏል
ሚኒስትሯ የህክምና ማዕከላት አዳዲስ በሽተኞችን ለመቀበል የሚያስችል ቦታም ሆነ አቅም እያጡ ነው ሲሉም ነው ያስታወቁት
በኢትዮጵያ ያለው የኮሮና ቫይረስ የስርጭት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የጤና ሚኒስትሯ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሯ የቫይረሱን ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው ባለፉት 12 ወራት ሁሉን ያሳተፈ መጠነ ሰፊ ስራ በመሰራቱ በቫይረሱ ምክንያት ሊደርስ ይችል የነበረውን አስከፊ ጉዳት በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ምላሹ እጅጉን በመቀዛቀዙ የበሽታው ስርጭት እጅግ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
እስካሳለፍነው አርብ ድረስ በነበሩት 10 ቀናት ውስጥ ከ8 ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውንም ዶ/ር ሊያ ታደሠ የገለጹት፡፡
ይህም ከዚህ ቀደም ከ9 እስከ 10 በመቶ የነበረው የበሽታው ምጣኔ በአማካይ ወደ 13 በመቶ ማደጉን የሚያሳይ ነው፡፡
ዶ/ር ሊያ የጹኑ ህክምና የሚፈልጉ ታማሚዎች ቁጥር ከአቅም በላይ እየሆነ መጥቷል ያሉ ሲሆን ህመምተኞችን በጤና ተቋም ደረጃ መርዳት እና መንከባከብ ከባድ ፈተና እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሯ የህክምና ማዕከላት አዳዲስ በሽተኞችን መቀበል የሚያስችል ቦታም ሆነ አቅም እያጡ ነው ሲሉም ነው ያስታወቁት፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ እና በሁሉም የክልል ከተሞች የሚገኙ የጽኑ ህመምተኛ ክፍሎች እየሞሉ እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡
“ሁሉም የመተንፈሻ መሳሪያዎች በህመምተኞች በመያዛቸው በሞትና በህይወት መካከል ሆነው የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ወረፋ የሚጠብቁ ህሙማን መኖራቸው ችግሩ ምን ያህል አስከፊ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ነው” ነው ዶ/ር ሊያ ያሉት፡፡
ባለፉት 10 ቀናት የ123 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ይህም በየቀኑ በአማካይ 12 ሰዎች በበሽታው ሲሞቱ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም ቁጥሩ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠላቸውን ታማሚዎች ብቻ የሚያሳይ ነው፡፡
ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ሚኒስትሯ ተደርገዋል ያሏቸው አነስተኛ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡
ቤት ውስጥ ህክምናቸውን የሚከታተሉ ሰዎች ህመሙ እስኪባባስ ድረስ ቤት ውስጥ ማሳለፋቸው ለጽኑ ታማሚዎች ቁጥር መጨመር ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል ሚኒስትሯ፡፡ ሆኖም ይህ ሊሆን አይገባውም ህመሙ ሲባባስ ወደ ህክምና ተቋማት መምጣትም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ይህ ሆኖ ሳለ የጥንቃቄው ነገር እየላላ ምጣቱንና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ነው የጠቆሙት፡፡
የሰርግ እና ሌሎች የማህበራዊ ስነ-ስርዓቶች ያለጥንቃቄ እየተከናወኑ መሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ እያደረገው ይገኛልም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዶ/ር ሊያ ከችግሩ ለመውጣት የሁሉም መተባበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ሁሉም ማስክ እንዲያደርግ የህግ አስከባሪ አካት ይሄን እንደዲመክሩና እንዲያስገድዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ትናንት ብቻ 1 ሺ 161 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ እስካሁን በአጠቃላይ 161 ሺ 974 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን 136 ሺ 443 ማገገማቸውንና 2 ሺ 391 ሰዎች መሞታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
እንደ አህጉር በአፍሪካ በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው በሚባልበት በአሁኑ ወቅት ነው ቁጥሩ በኢትዮጵያ እየጨመረ ያለው፡፡
በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር እንደ አህጉር ከባለፈው ወር በአማካይ የ15 በመቶ ቅናሽ እንዳለው የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) አስታውቋል፡፡
ዛሬ የበይነ መረብ ሳምንታዊ የጋዜጣዊ መግለጫ መርሃ ግብር የነበራቸው የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ በምስራቅ አፍሪካ ያለው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የ7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በወረርሽኙ ክፉኛ ተጠቅተው በነበሩት በእነ ደቡብ አፍሪካና ግብጽ ሳይቀር ሲቀንስ በኢትዮጵያ መጨመሩን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ የ7 በመቶ፣ በኬንያ የ6 በመቶ፣ በናይጄሪያ የ10 በመቶ ጭማሪ አሳይቷልም ብለዋል ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ፡፡