ከ3.8 ቢሊየን በላይ ሰዎች በ2050 ከልክ ላለፈ ውፍረት እንደሚጋለጡ ጥናት አመላከተ
ላንሴት የአለም የወፍራሞች ቀን ዛሬ ሲከበር የክፍለ ዘመኑ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ባለው ያልተመጣጠነ ውፍረት ዙሪያ አዲስ ጥናት ይፋ አድርጓል

በ204 ሀገራት የተደረገው ጥናት መንግስታት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል
ከአለም አዋቂ ህዝብ ውስጥ 60 በመቶ የሚጠጋውና ሲሶ የሚሆኑ ህጻናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች በ2050 ከልክ ላለፈ ውፍረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተነገረ።
የአለም የወፍራሞች ቀን ዛሬ ሲከበር ታዋቂው የህክምና ጆርናል ላንሴት አዲስ ጥናት ይፋ አድርጓል።
በፈረንጆቹ 1990 ከአለም ህዝብ ያልተመጣጠነ ክብደት ያለው 929 ሚሊየን ነበር። ይህ አሃዝ በ2021 ወደ 2.6 ቢሊየን ከፍ ብሏል።
መንግስታት የክፍለ ዘመኑን አሳሳቢ የጤና ችግር መቅረፍ ካልቻሉና አሁን ባለበት ፍጥነት ከቀጠለ ከ15 አመታት በኋላ አሃዙ ወደ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ከፍ እንደሚል የላንሴት ጥናት አመላክቷል።
በ204 ሀገራት የተሰበሰበ መረጃን መሰረት ያደረገው ጥናት በህጻናት ላይ ውፍረት የማጋጠም እድሉ በ121 በመቶ ከፍ ማለቱንም ነው የጠቆመው።
ከልክ ያለፈ ውፍረት የሀብታም ሀገራት ችግር ተደርጎ ቢታይም በተገላቢጦሽ ነው የሚለው ጥናቱ አነስተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን አብራርቷል።
በ2050 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ይደርሳል ተብሎ ከተተነበየው ወፍራም ህዝብ ውስጥ ሲሶው በመካከለኛው ምስራቅ፣ ሰሜን አፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን ይኖራሉ ተብሎ ተገምቷል።
ከ15 አመታት በኋላ ከፍተኛ የወፍራም ህዝብ ይኖርባቸዋል ከተባሉት ውስጥ ቻይና በ627 ሚሊየን ቀዳሚዋ ናት፤ ህንድ በ450 ሚሊየን እንዲሁም አሜሪካ በ214 ሚሊየን ይከተላሉ።
ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት በሚታይባቸው ከሳህራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ 522 ሚሊየን ህዝብ ላልተመጣጠነ ክብደት ሊጋለጥ ይችላል ተብሏል።
በናይጀሪያ ከልክ ያለፈ ውፍረት የሚኖርባቸው ሰዎች ቁጥር በ2021 ከነበረው ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሮ በ2050 141 ሚሊየን እንደሚደርስም ነው የላንሴት ጥናት ያመላከተው። ይህም ናይጀሪያን በርካታ ወፍራም ዜጎች ካለባቸው ሀገራት አራተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።
አጥኝዎቹ ክብደትን ለመቀነስ የሚወሰዱ መድሃኒቶችን ከግምት ውስጥ እንዳላስገቡ የገለጹ ሲሆን፥ መንግስታት እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ፈጣን መፍትሄዎችን እንዲተገብሩ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ2.3 ቢሊየን በላይ የአለማችን ህዝብ ከልክ ላለፈ ውፍረት የተጋለጠ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ ግማሹ የሚኖሩት በቻይና፣ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሜክሲኮ፣ ኢንዶኔዥያ እና ግብጽ ነው።
በ2050 ከሶስት ወጣቶች አንዱ ያልተመጣጠነ ክብደት ይኖረዋል ያለው የላንሴት ጥናት ዋነኛ አምራቹን ሃይል ለተለያዩ እክሎች የሚዳርገውን አሳሳቢ ጉዳይ አመጋገብን በማስተካከልና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በመከወን ለመቀነስ ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስቧል።