ውፍረትን ለመቀነስ ተብሎ የሚወሰድ መድሀኒት ለአይነ ስውርነት ሊዳርግ ይችላል ተባለ
ኦዜምፒክ እና ዊጎቪ የተሰኙት የሰውነት ክብደት መቀነሻ መድሀኒቶች በአይን ጤና ላይ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ተገልጿል
በሰዎች ላይ የሚታይ ፈጣን የክብደት መቀነስ የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚያመጣ የጤና ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል
ውፍረትን ለመቀነስ ተብሎ የሚወሰድ መድሀኒት ለአይነ ስውርነት ሊዳርግ ይችላል ተባለ።
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ በሚል የሚወሰዱ መድሀኒቶችን መጠቀም እየተለመደ መጥቷል።
በፍጥነት የሰውነት ክብደት እንዲቀንሱ ያደርጋሉ ከተባሉት መድሀኒቶች መካከል ኦዜምፒክ እና ዊጎቪ ዋነኞቹ ናቸው።
ሀርቫርድ ሜዲካል ዩንቨርስቲ በ17 ሺህ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት የአይን እይታ ችግር እንደሚያደርስ ፍንጭ ሰጥቷል።
ቢቢሲ ጥናቱን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው መድሀኒቱ በተለይም የስኳር ህመምተኞች አራት ዕጥፍ ለእይታ ችግር ተጋልጠዋል።
በሀርቫርድ ዩንቨርስቲ የጤና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጆሴፍ ሪዞ እንዳሉት ጥናቱ ለረጅም ዓመታት ሰዎች ሲወስዱት የቆየውን መድሀኒት ተያያዥ እና የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንደሚያመጣ አመላክቷል ብለዋል።
እንዲሁም በመድሀኒቶቹ ዙሪያ ሌሎች ጥናቶች እንዲደረጉ ፍንጭ የሰጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የክብደት መቀነሻ መድሀኒቶቹን የሚያመርተው ኖቮ ኖርዲስክ ጥናቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መድሀኒቶቹን በሚወስዱ ሰዎች ላይ ስለሚደርሱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ተጨማሪ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ ጥናትም በ2027 እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል ያለው ድርጅቱ አሁን ይፋ የተደረገው ጥናት ውጤት ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው አስታቋል።
መድሀኒቶች በባህሪያቸው ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ህመም እና ሌሎች የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንደሚያስከትሉ ይገመታል ተብሏል
የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው ክብደትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀነስ በሚል መድሀኒቶችን መውሰድ ትክክል አለመሆኑን ገልጸው በፍጥነት ብዙ ኪሎ ግራም ክብደት መቀነስ የጎንዮሽ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ አሳስበዋል።