ሴኔጋል በቀጣዩ ዓመት የኮሮና ክትባቶችን ማምረት ልትጀምር ትችላለች ተባለ
የኮሮና ክትባቶች የባለቤትነት ፈቃዶች ለጊዜው እንዲቆሙ ዓለም አቀፍ ጫና በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል
ክትባቶቹ የሚመረቱባቸው የአፍሪካ ሃገራት በቅርቡ እንደሚለዩ ተገልጿል
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች የሚመረቱባቸው ሃገራት በቅርቡ እንደሚለዩ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ሃገራቱን ከመለየት ባሻገር ክትባቶቹን እስከተያዘው የፈረንጆ ዓመት (2021) መጨረሻ ለማምረት የተቃረቡ አንዳንድ ሃገራት እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የትኞቹ ሃገራት እንደሆኑ በግልጽ አላስቀመጡም ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
ሮይተርስ ግን ሴኔጋል በቀጣዩ ዓመት ‘ዩኒቨርሴል’ ከተባለ የቤልጂዬም መድሃኒት አምራች ኩባንያ ጋር በመተባበር ክትባቶቹን ማምረት ልትጀምር እንደምትችል ዘግቧል፡፡
‘ዩኒቨርሴል’ በአፍሪካ ያለውን የክትባቶች አቅርቦት መጠን የማሳደግ ፍላጎት አለው፡፡ ለዚህም ሴኔጋል ዳካር ከሚገኘው የፓስተር የምርምር ተቋም ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ፓስተር የኩባንያውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ክትባቶችን ያመርታል፡፡
ተቋሙ በቀጣዩ ዓመት በኩባንያው የተመረቱ ክትባቶችን በሴኔጋል ማሰራጨት የሚጀምርም ሲሆን እ.ኤ.አ በ2022 አጋማሽ ሙሉ ምርት እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ሞደርና እና ፋይዘርን ጨምሮ ሌሎችም የኮሮና ክትባት አምራች ተቋማት የእውቀትና ምርምር ስራዎቻቸውን ለአፍሪካ ሃገራት እንዲያጋሩ እና ክትባቶቹ እንዲመረቱ ጠይቀዋል፡፡
ከክትባቶች የፈጠራ መብት ጋር በተያያዘ ብዙ ብዙ ነገሮች ሲባሉ ቆይተዋል፡፡ በሃገራት መካከል ባለው የአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠሩ ኢ-ፍትሐዊ የተደራሽነት ችግሮች እንዲቆሙ ሲጠየቁም ተሰንብቷል፡፡
በተለይም እንዲህ እንደ ኮሮና ዓይነት መላ የዓለም ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ ወረርሽኞች ሲያጋጥሙ ወረርሽኞቹን ለማስቆም በሚያስችሉ የፈጠራና የምርምር ስራዎች ላይ የባለቤትነት መብቶች ክልከላ እንዳይኖር እየተጠየቀ ይገኛል፡፡
ያደግን ነን ባይ ሃገራት በክትባቶቹ ላይ የያዙትን የባለቤትነት እና የአቅርቦት የበላይነት አቁመው የወረርሽኙ ክትባቶች አፍሪካ እና እስያን ጨምሮ በተለያዩ የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ተመርተው በፍትሐዊነት እንዲሰራጩ ከፍተኛ ግፊት በመደረግም ላይ ነው፡፡