ክትባቱ ከቻይናው መድሃኒት አምራች ኩባንያ ‘ሲኖ ፋርም’ ጋር በመተባበር የተመረተ ነው ተብሏል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) “ሃያት ፋክስ” የተሰኘ የኮሮና ቫይረስ ክትባት አመረተች፡፡
ክትባቱ በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን የመዋጋቱን ተግባር በይፋ የተቀላቀሉ ክትባቶችን ጎራ ተቀላቅሏል ተብሏል፡፡
“ሃያት ፋክስ” ከቻይናው መድሃኒት አምራች ኩባንያ ‘ሲኖ ፋርም’ ጋር በመተባበር መቀመጫውን አቡዳቢ ባደረገው ቡድን 42 (G42) የሰው ሰራሽ አስተውሎ ተቋም የተመረተ የኮሮና ክትባት ነው፡፡
ይህም በባህረ ሰላጤው ቀጣና የተመረተ የመጀመሪያው የኮሮና ክትባት ያደርገዋል፡፡
ዩኤኢ ለኮሮና ወረርሽኝ የሚሆን ክትባት ማምረቷን ከሰሞኑ አስታውቃ ነበር፡፡ ይህም ትልቅ እርምጃ ሆኖ በሃገሪቱ ታሪክ ተመዝግቧል፡፡
G42 ባሳለፍነው ዓመት ከሲኖ ፋርም ጋር በመተባበር የኮሮና ክትባቶች የ3ኛ ዙር ክሊኒካዊ ሙከራን በተለያዩ አረብ ሃገራት ሲያደርግ ነበረ፡፡
ሙከራው ከ125 የተለያዩ ሃገራት የተውጣጡ ከ45 ሺ በላይ በጎ ፍቃደኞችን አሳትፏል፡፡
“ሃያት ፋክስ” የሚመረትበት ፋብሪካ በኸሊፋ ኢንዱስትሪ መንደር የሚገኝ ሲሆን በዚህ ዓመት ወደ ስራ ይገባል ተብሏል፡፡
ፋብሪካው በዓመት 200 ሚሊዬን ክትባቶችን የማምረት አቅም እንዳለው ነው የተነገረው፡፡
ሆኖም “ሃያት ፋክስ” እስከዚያው ድረስ ጁልፋር በተሰኘው የመድሃኒች አምራች ኩባንያ በዚያው በዩኤኢ ይመረታል ተብሏል፡፡
ጁልፋር በወር እስከ 2 ሚሊዬን ዶዝ እንደሚያመርትም ነው የተነገረው፡፡
ሲኖፋርም ይፋ እንዳደረጋቸው ቅድመ መረጃዎች ከሆነ “ሃያት ፋክስ” 79.34% ያህል የኮሮና ቫይረስን የመዋጋት ዐቅም አለው፡፡