እስራኤል በጋዛ አጥብቃ የምትፈልጋቸው ሶስት የሃማስ መሪዎች እነማን ናቸው?
የሃማስ ወታደራዊ መሪዎች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ሲደረስ እና የእስረኛና ታጋች ልውውጥ ሲደረግ ቁልፍ ሚና ነበራቸው ተብሏል
ለሰባት ቀናት ጋብ ብሎ የነበረው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ዳግም አገርሽቷል
ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከሰባት ቀናት ተኩስ አቁም በኋላ ዳግም ተቀስቅሷል።
የእስራኤል ጦር ሃማስን ሙሉ በሙሉ ካልደመሰስኩ ጦርነቱ አይቆምም በሚለው አቋሙ እንደጸና ነው።
ሬውተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ቴል አቪቭ የሃማስን ዋና ዋና አዛዦች ካልገደለች ዘመቻዋ እንደማታቋርጥ ይታመናል።
በዋናነትም ሶስት የቡድኑን ወታደራዊ መሪዎች በማደን ላይ መሆኗ ነው የተነገረው።
በእስራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው የሚገኙት የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ አዛዡ መሀመድ ዴይፍ፣ ምክትሉ ማርዋን ኢሳ እና በጋዛ የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ናቸው።
ሶስቱ ግለሰቦች ሚስጢራዊ ወታደራዊ ምክርቤት አቋቁመው የጥቅምት 7ቱን ጥቃት መምራታቸው ይነገራል።
በኳታር አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ የእስረኞች እና ታጋቾች ልውውጥ ሲደረግም የሶስቱ መሪዎች ሚና ከፍተኛ ነበር ተብሏል።
እስራኤል እነዚህ የሃማስ ቁልፍ አመራሮች በቁጥጥር ስር ማዋል ወይም መግደል ጦርነቱ አድማሱን እንዲያጠብ ያደርገዋል የሚል እምነት እንዳላትም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንትም ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ሶስቱ የሃማስ መሪዎች መደምሰሻቸው በጣም ቅርብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ይሁን እንጂ ሃማስ በጋዛ ምድር ውስጥ ለአመታት በገነባው ውስብስብ ዋሻ ውስጥ እንደሚኖሩ የሚታመኑትን መሪዎች ለመያዝ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ተንታኞች ያነሳሉ።
መሪዎቹን በቤት ለቤት አሰሳ ለመግደል የሚደረግ ጥረትም የበርካታ ፍልስጤማውያን እና የእስራኤል ወታደሮችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችልም ነው የሚገለጸው።
እስራኤል የሃማስ መስራቹን ሼክ አህመድ ያሲንና የቀድሞ የቡድኑን መሪ አብደል አዚዝ አል ራንቲሲን በ2004 ብትገድልም አዳዲስ መሪዎች ቡድኑን አስቀጥለውታል የሚሉ ተንታኞች የሶስቱ የጋዛ የሃማስ መሪዎች ግድያም የቡድኑን ህልውና እንዲያከትም አያደርገውም ባይ ናቸው።
የከሸፉ የግድያ ሙከራዎች
ሶስቱም የሃማስ መሪዎች በእስራኤል ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች ተደርጎባቸዋል።
ከ2021 በፊት ሰባት ጊዜ የግድያ ሙከራ የተደረገበት ሞሀመድ ዴይፍ አንድ አይኑን አጥቷል፤ በእግሩ ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። እስራኤል በ2014 በፈጸመችው የአየር ድብደባም ሚስቱ እና የሶስት አመት ሴት ልጁ መገደላቸውይታወሳል።
በአደባባይ ተቃውሞዎች የማይጠፋው ያህያ ሲንዋርም የእስራኤልን ጥቃት ፍራቻ ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች መጠቀም ካቆመ አመታት ተቆጥረዋል።
“ጥላቢሱ ሰው” የሚል ቅጽል ስም የወጣለውት ማርዋን ኢሳም እንደ ዴይፍ እና ሲንዋር ታዋቂ ባይሆንም ባለፉት አመታት የሃማስ ውሳኔዎች ቁልፍ ድርሻ ነበረው፤ አንደኛቸው ቢያልፉ እንዲተካቸውም ዝግጁ ተደርጓል።
ሶስቱም በእስራኤል በጥብቅ የሚፈለጉት የሃማስ መሪዎች በስደተኞች ካምፕ ተወልደው በእስራኤል እስርቤቶችም ለአመታት ያሳለፉ ናቸው።