ወታደራዊ ክንፉ ሃማስ በፍልስጤማውያን ዘንድ ተቀባይነቱ ከፍ እንዲል ማድረጉ ይነገራል
በፈረንጆቹ 1987 በሺሼክ አህመድ ያሲን የተመሰረተው ሃማስ 1993ቱን የኦስሎ ስምምነት ተቃውሞ ነፍጥ ካነገበ ሶስት አስርት አመታት ተቆጥረዋል።
ስምምነቱ እስራኤል ህገወጥ ሰፈራዋን እንድታስፋፋ እድል የፈጠረ ነው ያለው ሃማስ በ1992 ራሱን የቻለ ወታደራዊ ክንፍ አቋቁሟል።
በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ ለቡድኑ ሲዋጉ የቆዩ ታጣቂዎችን በአንድ ላይ ያደራጀበትን ወታደራዊ ክንፍም “ቃሳም ብርጌድ” የሚል ስያሜ ሰጠው።
በሞሃመድ ዴይፍ የሚመራው “ቃሳም ብርጌድ” በእስራኤል ላይ የፈጸማቸው ጥቃቶች ሃማስ በፍልስጤማውያን ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረጉ ይነገራል።
ሲአይኤ ወርልድ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው “ቃሳም ብርጌድ” ከ20 እስከ 25 ሺህ የሚጠጉ ተዋጊዎች እንዳሉት ይገመታል፤ ምንም እንኳን አሃዙ አከራካሪ ቢሆንም።
እስራኤል በፈጸመቻቸው የአየር ድብደባዎች በሺዎች የሚቆጠ/ሩ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ በተለይ እስራኤል በ2005 የጋዛ ሰርጥን ለቃ ከወጣች በኋላ በሰው ሃይልም በጦር መሳሪያም እየተጠናከረ መሄዱን ነው ተንታኞች የሚገልጹት።
ከኢራን የሚያገኘው የፋይናንስ ድጋፍም የጦር መሳሪያዎችን በራሱ እንዲያመርት እድል መፍጠራቸው ተነግሯል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች እና ድሮኖችን ታጥቋል የተባለው “ቃሳም ብርጌድ” ሃማስ ከ20 ቀን በፊት በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲከፍት ሮኬቶችን አዝንቧል።
ከሰሞኑም በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት ፈጽሜባቸዋለው ያላቸውን ድሮኖች አሳይቷል።
“ቃሳም ብርጌድ” ሮኬቶች፣ ፈንጂዎች፣ ጸረ ታንክ ሚሳኤሎች እና ሞርታሮችን የሚሰሩ በርካታ ባለሙያዎች አሉት።
የሃማስ ተዋጊዎች ከእይታ ውጭ እንዲንቀሳቀሱም የምድር ውስጥ መንገድ እና መደበቂያዎችን በመስራት ትልቅ ድርሻ አለው ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2021 ያወጣው ሪፖርት “ቃሳም ብርጌድ” እና ሌሎች የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች በ2021 ብቻ ከ4 ሺህ 400 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሰዋል ይላል።
የሃማሱ “ቃሳም ብርጌድ” እና እንደ ኢስላሚክ ጂሃድ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች በአሁኑ ጦርነትም እስራኤል ላይ በጋራ ተባብረው ጥቃት ለማድረስ እየሞከሩ ነው።
ቴል አቪቭ በቡድኑ ዋና ዋና ይዞታዎች (የጦር መሳሪያ ማምረቻና ማከማቻዎች) ላይ የምታደርሰው የአየር ድብድባ ግን ጦርነቱ እንደተጀመረ ያደርሱት የነበረውን አይነት ጥቃት እንዳያስቀጥሉ እያደረጋቸው ይመስላል።