የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ስምምነቱ ባለቀ በሰአታት ውስጥ 109 ሰዎች ተገድለዋል፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ቆስለዋል
ለበርካታ ሳምንታት ሲዋጉ የነበሩት እስራኤል እና ሀማስ በኳታር አደራዳሪነት ተኩስ ለማቆም ከተስማሙ በኋላ የተወሰኑ ቀናት በጋዛ ምድር የተኩስ ድምጽ ቆሞ ነበር።
በሀማስ የታገቱ እስራኤላውያን እና በእስራኤል ታስረው የነበሩ ፍልስጤማውያን እንዲለቀቁ ያስቻለው ለሁለት ጊዜ የተራዘመው ተኩስ አቁም ስምምነት በትናንትናው እለት ተጥሷል።
እስራኤል ሮኬት በማስወንጨፍ ሀማስ ተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሷል የሚል ክስ አሰምታለች።
ተኩስ አቁሙ መጣሱን ከገለጸች በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት በርካታ ፍልስጤማውያን የመቁሰል እና የሞት አደጋ እንደደረሰባቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
በደቡባዊ ጋዛ የምትገኘው ካን ዮኒስ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባታል ተብሏል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ስምምነቱ ባለቀ በሰአታት ውስጥ 109 ሰዎች ተገድለዋል፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ቆስለዋል።
ከጋዛ ሮኬቶች ሲወነጨፉ በደቡባዊ እስራኤል የጥቃት ማስጠንቀቀመያ ደወል ድምጽ ተሰምቷል።
በሌላ ግንባር የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ፍልስጤምን ለመደገፍ በሰሜን በኩል ወደ እስራኤል መተኮሱን አስታውቋል።
አሜሪካ ስምምነቱን በመጣስ የፍልስጤሙን ሀማስ ብትከስም፣ እስራኤል እና ሀማስ ግን ስምምነቱን በመጣስ እርስበእርስ እየካሰሱ ይገኛሉ።
ተመድ ውጊያው በጋዛ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ ያባብሰዋል ብሏል።
የተመድ የሰብአዊ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ ጀንስ ላርኬ "ሲኦል ወደ ጋዛ እየተመለሰ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል አሁንም ሃማስን የማጥፋት እቅዷን እንዳልተወች ገልጻለች።