በአሜሪካ ዋይት ሀውስ አቅራቢያ በመብረቅ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ
በአሜሪካ በመብረቅ አደጋ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው ተብሏል
በአሜሪካ በዓመት 40 ሚሊየን የመብረቅ አደጋዎች ይከሰታሉ
በአሜሪካ ዋይት ሀውስ አቅራቢያ በመብረቅ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ።
በዋሸንግተን ነጩ ቤተ መንግስት አቅራቢያ በተፈጠረ የመብረቅ አደጋ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ አንድ ሰው ደግሞ ክፉኛ ቆስሏል ተብሏል።
በአሜሪካ አሁን ላይ እየተመዘገበ ያለው ሙቀት ባለፉት 30 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።
በከፍተኛ ሙቀት እና ቅዝቃዜ አየር መጋጨት ምክንያት እንደሚፈጠር የሚገለጸው መብረቅ በአሜሪካ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነ የሀገሪቱ የአየር ንብረት አገልግሎት ማዕከልን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ተቋሙ ጥናት ከሆነ በአሜሪካ በዓመት በአማካኝ 40 ሚሊዮን የመብረቅ አደጋ የሚደርሱ ሲሆን አብዛኞቹ በሰዎች ላይ አደጋ አያደርሱም ተብሏል።
አላስካ እና ካሊፎርኒያ ግዛቶች በአንጻራዊነት ብዙ የመብረቅ አደጋዎች የሚደርስባቸው ግዛቶች ሲሆኑ፤ ፍሎሪዳ ደግሞ ብዙ ሰዎች በመብረቅ አደጋ የሚሞቱበት ግዛት ነው ተብሏል።
የመብረቅ አደጋ ከሚደርስባቸው ሰዎች መካከል 90 በመቶዎቹ ከአደጋው የሚተርፉ ሲሆን ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ 444 ሰዎች በዚሁ መብረቅ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከአሜሪካ ውጪም ብራዚል እና ህንድ በአንጻራዊነት ብዙ የመብረቅ አደጋዎች የሚደርስባቸው ሀገራት ናቸው።