በህንድ በ24 ሰዓት ውስጥ በደረሰ የመብረቅ አደጋ የ38 ሰዎች ህይወት አለፈ
11 ሰዎች በእጅ ስልካቸው ሰልፊ ፎቶ በመነሳት ላይ እያሉ ህይወታቸው ያለፈው
በህንድ በ2019 ብቻ በደረሱ የመብረቅ አደጋዎች የ2 ሺህ 900 ሰዎች ህይወት አልፏል
በህንድ በተለያዩ ግዛቶች በ24 ሰዓታት ውስጥ በደረሱ መብረቅ አደጋዎች የ38 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በራጃስታን ግዛት ምእራባዊ ክፍል ሲሆን፤ በ12ኛ ከፍለ ዘመን እንደተገነባ በሚነገርለት ‘አምበር ፎርት’ በተባለ ታሪካዊ ስፍራ ላይ የነበሩ 11 ሰዎች መሆናቸውን ኤ.ፒ ኒውስ ዘግቧል።
አናንድ ስሪቫስታቫ የተባሉ ከፍተኛ የፖሊስ አዛዥ እንደተናሩት ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቻቸው በእጅ ስልካቸው ሰልፊ ፎቶ በመነሳት ላይ የነበሩ ናቸው።
በራጃስታን ግዛት ሌላ አካባቢ ላይ የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ በደረሰ የመብረቅ አደጋም ተጨማሪ የ9 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና 20 ሰዎች መጎዳታቸውንም አስታውቀዋል።
በኡታ ፓርዴሽ ግዛት ትናንት በደረሰ የመብረቅ አደጋም የ18 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎችም በግብርና ስራ ላይ የነበሩ መሆናቸውን የአካባቢው ከፍተኛ ባለስልጣን ማኖጅ ዲክሲት ተናግረዋል።
ሁለቱም የህንድ ግዛቶች በመብረቅ አደጋው ህይወታቸው ላለፈ ሰዎች ቤተሰቦች የካሳ ክፍያ እንደሚሰጡ መግለጻቸውም ተነግሯል።
በቀጣይ ሁለት ቀናትም በህንድ የተለያዩ ግዛቶች ከፍተኛ የሆኑ መብረቅ አደጋዎች ሊደርሱ እንደሚችሉ የሀገሪቱ ሜትሪዮሎጂ ቢሮ አሳስቧል።
በህንድ ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉ ወራቶች መብረቅ አደጋዎች የተለመዱ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ብቻ በህንድ የተለያ ግዛቶች በደረሱ የመብረቅ አደጋዎችም የ2 ሺህ 900 ሰዎች ህይወት ማለፉን መጃዎች ያመለክታሉ።