በኢራን በጎርፍ አደጋ 53 ሰዎች ተገደሉ፤ ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች እየተፈለጉ ነው
በአደጋው ብዙ አውራ ጎዳናዎች ተዘግተዋል
የነፍስ አድን ሰራተኞች የጠፉትን በመፈለግ ላይ መሆናቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል
ባለፈው አርብ ኢራን ውስጥ በከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ በትንሹ 53 ሰዎች ሞተዋል፡፡
የነፍስ አድን ሰራተኞች የጠፉትን በመፈለግ ላይ መሆናቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የቀይ ጨረቃ ማህበር የአደጋ ጊዜ ስራ ሃላፊ የሆኑት መህዲ ቫሊፑር ለመንግስት ቲቪ እንደተናገሩት ከሁለት ቀናት የጎርፍ አደጋ በኋላ የጠፉ 16 ሰዎች እስካን ድረስ አልተገኙም፡፡ የጎርፍ አደጋው የተከሰተው ኢራን ካሏት 31 ግዛቶች ውስጥ በ18 ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ 400 ከተሞች እና መንደሮች።
በአደጋው ብዙ አውራ ጎዳናዎች ተዘግተዋል።
በቴህራን ሰሜናዊ ምስራቅ የአልቦርዝ ተራሮች ግርጌ ላይ ቢያንስ 10 ሰዎች መሞታቸውን የቴህራን ገዥ ሞህሰን ማንሱሪ ለመንግስት ቲቪ ተናግረዋል።
አርብ ዕለት በቴህራን ግዛት ሰሜናዊ አካባቢዎች የጎርፍ መጥለቅለቅ እየደረሰ መሆኑን ገልፀው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ቢደረጉም ተጓዦች አሁንም ወደ ፊሩዝ ኩህ እያመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ከቴህራን 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የፍሩዝ ኩህ ከተማ በቀዝቃዛው የበጋ ሙቀት ምክንያት ለእረፍት ለሚመጡ ሰዎች ተወዳጅ ማረፊያ ነች፡፡ የአካባቢው ለምለም መንገዶችም በተጓዦች ዘንድ ተወዳጅ ናቸው።
ከቴህራን ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘው ኢማምዛዴህ ዳቮድ መንደር በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ቢያንስ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል። እስከ 14 የሚደርሱ ሰዎች መጥፋታቸው ተነግሯል።
ባለፈው ቅዳሜ በደቡብ ፋርስ ግዛት በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ22 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡