የቡድን 7 አባል ሀገራት መሪዎች ለደሃ ሀገራት 1 ቢሊየን የኮቪድ ክትባት ለመስጠት ቃል ገቡ
ክትባቶቹ በቀጥታ አሊያም በኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት ለሀገራቱ እንዲደርሱ ይደረጋል ተብሏል
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እስከ 2050 ድረስ የካርቦን ልቀትን ወደ ዜሮ ለማውረድ ተስማምተዋል
የቡድን 7 አባል ሀገራት ለደሃ ሀገራት 1 ቢሊየን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባ ለመስጠት ቃል መግባቸው ተሰምቷል።
ቡድን 7 የዓለማችን ባለጸጋ ሀገራት በእንግሊዝ ኮርንዌል የባህር ዳርቻ ከተማ ዓመታዊ ጉባዔያቸውን አካሂደዋል።
በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ የዓለም ባለ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሀገራት ለደሃ ሀገራ 1 ቢሊየን ዶዝ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ለመስጠት ቃለ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ይህም የዓለም ህዝብን ለመከተብ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በልገሳ የሚሰጠው ክትባት በቀጥታ አሊያም በዓለም ጤና ድርጅት ኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት ለሀገራቱ እንዲደርስ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
ከዚህም ውስጥ ብሪታኒያ 100 ሚሊየን ክትባቶችን ለደሃ ሀገራት እንደምትሰጥም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ያስታወቁት።
የጉባዔውን መጠናቀቅ ተከትሎ በወጣው መግለጫ፤ ወረርሽኙ በአጠረ ጊዜ ውስጥ እንዲቆም እና ዓለምን ለቀጣይ ጊዜ ለማዘጋጀት እንዲቻል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በአስቸኳይ ክትባት እንዲያገኙ በትብብር እና በፍጥነት ሊሰራ እንደሚገባ የሀገራቱ መሪዎች ከስምምነት መድረሳቸው ተመላክቷል።
እንዲሁም የከባቢ አየር ለውጥን ለመከላከል በፈረንጆቹ እስከ 2050 ድረስ የካርቦን ልቀትን ወደ ዜሮ ለማውረድ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።