ልዩልዩ
የቻይናው ሲኖፋርም የኮቪድ 19 ክትባት በዓለም ጤና ድርጅት እውቅና ተሰጠው
ሲኖፋርም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች በ2 ዶዝ የሚሰጥ የክትባት ዓይነት ነው
የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ ቀደም ፋይዘር፣ አስትራ ዜኒካ፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንና ሞደርና ለተባሉ ክትባቶች እውቅና መስጠቱ ይታወሳል
የዓለም ጤና ድርጅት የቻይናው ሲኖፋርም ኩባንያ ላመረተው የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት የድንገተኛ አገልግሎት እውቅና ሰጠ።
ድርጁቱ ከምእራባውያን ሀገራት ውጪ ለመተረተ የኮሮና ክትባት እውቅና ሲሰጥ የመጀመሪያው ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ሲኖፋርም ክትባት አሁን ላይ እውቅና ቢሰጥም ክትባቱ ግን በቻይና እና በሌሎች የዓለም ሀገራት በሚሊየን ለሚቆጠሩ ሰዎች መሰጠቱ ይታወቃል።
በተለይም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካ እና የእሲያ ሀገራት ክትባቱን በራሳቸው ፈቃድ ጥቅም ላይ ማዋል ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል።
ከቆይታ በኋላም ቢሆን የዓለም ጤና ድርጅት በትናነትናው እለት የሲኖፋርም የኮቪድ 19 ክትባት ክትባት ደህንነት፣ ጥራት እና ውጤታማነት ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ድርጅቱ አክሎም የሲኖፋርም የኮቪድ 19 ክትባት ለጤና ባለሙያዎች እና ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባን ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ያግዛልም ብሏል።
ሲኖፋርም የኮቪድ 19 ክትባት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች በሁለት ዶዝ ሊሰጥ እንደሚገባም ነው የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀው።
ድርጅቱ በሌላኛው ‘ሲኖቫክ’ የተባለ ክትባት ላይ በቀናቶች ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ሩሲያውን ስፑትኒክም እየፈተሸ መሆኑም ተነግሯል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ ቀደም ለፋይዘር፣ አስትራ ዜኒካ፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን እና ሞደርና ለተባሉ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባቶች እውቅና መስጠቱ ይታወሳል።