“ከአካባቢያችን ውጡልን ብለው ነው ሰዎችን ያረዷቸው” የጉራፋርዳ ጥቃት ሰለባዎች
ነዋሪዎቹ ግድያውን የፈጸሙት ሰዎች የቀብር ስነ ሥርዓት እንዳይካሄድ መከልከላቸውንም ተናግረዋል
በጉራፋርዳ ነዋሪዎች የብሄር ማንነትን መሰረት አድርጓል ባሉት ጥቃት የ31 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የአካባቢው መንግስት ገልጿል
በጉራፋርዳ ነዋሪዎች የብሄር ማንነትን መሰረት አድርጓል ባሉት ጥቃት የ31 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የአካባቢው መንግስት ገልጿል
በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ሹፒና ድኒቃ ቀበሌዎች በርካታ ግለሰቦች መገደላቸውን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱን ነዋሪዎች ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ዜጎች የአማራ ተወላጆች መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል፡፡ ከተፈጸመው ግዲያ ባለፈም ዜጎቹ ያፈሩት ሀብትና ንብረት መውደሙን ተናግረዋል፡፡ አስተያየቱን ለአል ዐይን የሠጠው ይመር አሊ በአካባቢው ለስምንት ዓመት ያህል መኖሩን ገልጾ አሁን ግን “ከቀያችን ውጡልን” የሚል ነገር መምጣቱን አንስቷል፡፡
“እኛ በአካባቢው በሥራ ተሰማርተን ራሳችንን እና አካባቢውን ከመለወጥ ውጭ ምንም ችግር አልፈጠርንም” የሚለው ይመር “ይህንን ግድያ የፈጸሙት ሰዎች ዕድርተኞቻችን ነበሩ” ብሏል፡፡ አቶ ይመር እርሱ አምልጦ ህወቱን ማትፈሩን ገልጾ የነዋሪዎች ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ግልጿል፡፡ የተገደሉት ዜጎች ቀብር ላይ ሆኖ በስልክ አስተያየቱን የሰጠው አቶ አህመድ በበኩሉ አንድ የሸኮ ብሔር ተወላጅ ሌላ የሸኮ ብሄር ተወላጅን ከገደለ በኋላ ግዲያውን የፈጸመው የአማራ ብሔር ተወላጅ ነው በማለት ግዲያ መጀመሩን ይገልጻል፡፡
በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን የገለጸው አቶ አህመድ ቤቶቹን ቢንዚን በማርከፍከፍ ጭምር እያቃጠሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ይመር እንደገለጸው ሁሉ አቶ አህመድም “ከሀገራችን ውጡልን“የሚል ዘመቻ በማንገብ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያዎች እንደነበሩ ነው ለአል ዐይን የተናገረው፡፡ ሁለቱ አስተያየት ሰጭዎች በጫካ እና በየቅጠሉ ሥር በመሆን ሕይወታቸው ማትረፋቸውን ተናግረዋል፡፡
የተገደሉ ሰዎችን የቀብር ስነስርዓት ለማከናወን እንኳ ሳይቻል ቀርቶ ዛሬ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ግድያውን የፈጸሙት ሰዎች ቀብር ላይ ጭምር እየመጡ ጥቃት እያደረሱ ነውም ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ፡፡
ግድያውን በመፈጸም የተጠረጠሩ 16 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው የሚታወስ ሲሆን ነዋሪዎቹ ግን ይህ ስለመሆኑ እርግጠኞች እንዳልሆኑና ይያዛሉ ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል አንድ የፖሊስ አባልና አራት የሥራ አመራሮች መኖራቸውን ገልጸው ነበር፡፡
ዋና አስተዳዳሪው በወረዳው ጥቅምት 8 እና ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም በሁለት ቀበሌዎች በተፈፀመ ጥቃት የ31 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና አምስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸው1 ሺህ 480 አባወራዎች ተፈናቅለው በቢፍቱ ከተማ መጠለላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ፣የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬዓለም ሽባባው፣ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄነራል አደም መሐመድ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ከተፈናቀሉ ዜጎችና ጉዳት ከደረሰባቸው ተወካዮች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው፡፡
በ2005ዓ.ምበቤንች ማጂ ዞን ተመሳሳይ ማንነትን መሰራት ያደረገ ግድያና ማፈናቀል ተከስቶ ነበር፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች ለፌደራል መንግስት አቤቲታ አቅርበው ነበር፤ ክስም መስርተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡