ጥቃቱ “ከተራ ግጭት ይልቅ ስልታዊ በሆነ እና በመንግሥታዊ መዋቅር ጭምር የተደገፈ የሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊት” ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል
ከሰሞኑ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በተፈጸመው ጥቃት ከ160 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን አብን አስታወቀ
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ከሰሞኑ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ160 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን አስታወቀ፡፡
ተጨባጭ መረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን ያስታወቀው ንቅናቄው “ጥቃቶቹ ማንነትን መሰረት አድርገው የተፈፀሙ ናቸው” ብሏል፡፡
በተለይም ባለፉት 2 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በክልሉ ባለው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረገው “የዘር ማፅዳትና ሰብዓዊ ጥቃት” ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ቀጥሏል ያለም ሲሆን “ጥቃቱ ከተራ የማኅበረሰቦች ግጭት ይልቅ ስልታዊ በሆነ እና በመንግሥታዊ መዋቅር ጭምር የተደገፈ የሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊት” መሆኑን እንደሚያምን ገልጿል፡፡
ፎቶ፡ የንቅናቄው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
የክልሉ መንግሥት መረጃ እና ጥሪ እየቀረበለት ባለመድረሱ፤ የፌዴራል መንግሥቱም ባለው የደኅንነት መረጃ ተመርኩዞ ጥቃቱን ለመከላከል ፈጥኖ እርምጃ ባለመውሰዱ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም ከአሁን በኋላ መሰል ጥቃቶችን እንደማይታገስ ያስታቀው ንቅናቄው ለችግሩ ተባባሪ የሆኑ የክልሉ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በሕግ እንዲጠየቁ፣በክልሉ ለሚኖረው የአማራ ሕዝብ አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ፣ በፖሊስና በደኅንነት መዋቅሮች ውስጥ የመሳተፍ መብቱ እንዲከበር እና የክልሉ መዋቅር የነዋሪዎቹን መብቶች በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲከለስ አሳስቧል፡፡
የፌደራል መንግሥቱና ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በአማራው ሕዝብ ላይ በሚፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ላይ አሳይቷል ያለውን “ዳተኝነት” እንዲያቆምና ችግሩን ለመከላከልና ከመሰረቱ ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግስት ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ የሰጠው ይፋዊ መግለጫም ሆነ የጉዳቱን መንስዔና መጠን የሚያመለክቱ አሃዛዊ መረጃዎች የሉም፡፡
ሆኖም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የሰላም ሚኒስትሯን ሙፈሪያት ካሚልን ያካተተ ከፍተኛ የባለስልጣናት ልዑክ ጥቃቱ ወደተፈጸመባቸው አካባቢዎች ተጉዞ በጥቃቱ ምክንያት ሰላባ ከሆኑና ከተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይቷል፡፡
ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ፣በቸልተኝነትና በእንዝላልነት ጥቃቱ እንዲፈጸም ባደረጉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳልም ብሏል፡፡
ያለፉትን ሁለት ቀናት በስራ አስፈጻሚ ደረጃ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከሩን ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው አብን በአማራ ክልል በዝናብ ምክንያት በተፈጠሩ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋዎች ተጎጂ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል፡፡