የአማራ ተወላጆች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሁሉም መዋቅሮች እንዲካተቱ ስምምነት ላይ ተደረሰ
ከጥቃቱ በኋላ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ መግባባት ላይ ተደርሷል
ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት መረጃው የደረሳቸው የቀበሌ አመራሮች የራሳቸውን ቤተሰብ በማሸሽ ሌላው እንዲጎዳ ማድረጋቸውን የአማራ ክልል ገልጿል
የአማራ ተወላጆች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሁሉም መዋቅሮች እንዲካተቱ ስምምነት ላይ ተደረሰ
ባለፉት ዓመታት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን ንጹሃን በታጣቂዎች በሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት ለህልፈት ህይወት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡
ለአብነትም ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ የ14 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት ደግሞ በወምበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እና በቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት የንጹኃን ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡
የክልሉ ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ ድርጊቱ የተፈጸመው “ጸረ ሰላም” ሃይሎች በፈጸሙት ጥቃት የንጹኃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን “አረጋግጫለሁ” ብሎ ነበር፡፡
በመተከል ዞን እየተከሰቱ ያሉ ግድያዎችን በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ዋና አስተደዳሪው አቶ አንኩት ሽቱ እንዳሉት ለግድያዎቹ ምክንያት የሆኑት ተጠቃሚዎቸ አይደለንም ብለው የሚያስቡ ሰዎች በፈጠሩት ችግር ነው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዋናነት ከጸጥታ ተቋማት በስነ ምግባርና በአቅም ማነስ የወጡ ሰዎችን በማሰባሰብ ችግር እንዲፈጠር ያደረገው የጉሙዝ ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ተባባሪና የድርጊቱ አቀናባሪ የሆነው ህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ መሆኑንም ነው ዋና አስተዳዳሪው ለአል ዐይን ያስታወቁት፡፡
በወምበራ ወረዳ ኮንግ ማዕከል “የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስት ደጋፊ ናችሁ በሚል” በህብረተሰቡ ላይ የግድያ፣ የማገት እና የማፈናቀል ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ደግሞ የክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮ መግለጹ ይታወሳል፡፡
በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግድያዎች ህወሃት ከጀርባ አለ የሚለው ነገር በምን ማስረጃ ነው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና አስተዳዳሪው እኛ ህወሃት ነን የሚሉ ሰዎች በይፋ ተናግረው ግጭቱ ሲከሰት ሌሎቹ ለማምለጥ ሲሞክሩ እነርሱ ግን ተረጋግተው እየኖሩ ነበር፡፡ በዚህና በሌሎች ማስረጃዎች ህወሃት ከጀርባ መኖሩን እርግጠኞች ነን ብለዋል፡፡ህወሃትም ሆነ ሌላ ድርጅት ከጥቃቱ ጀርባ ኖረም አልኖረም ክልሉ ለምን ሰላምና ጸጥታውን አያስጠብቅም ስንል ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ አትንኩት አካባቢው ከፍተኛ የልማት ስራ የሚከናወንበት በመሆኑ ውስብስብ ነው ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ በአካባቢው የተከሰተው ግጭት አሊያም ተራ ሁከት አይደለም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ይህ እንደ ሽብር የሚቆጠር ድርጊት ነው በጥቅሉ ጭፍጨፋ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ላይ መከተል ዞንን የጦር አውድማ ለማድረግ የታሰበ ድርጊት እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ አትንኩት አካባቢው በከፍተኛ ደረጃ የልማት ኮሪደር በመሆኑ ያለውን ችግርና ግድያ ክልሉ ብቻ አያጠራውም የፌዴራል መንግስት እገዛም ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተካሄደው የዘር ተኮር ጥቃት መሆኑን በመግለጽ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩትም ድርጊቱ ጭፍጨፋ እንጅ ተራ ግጭት አይደለም በሚል የገለጸ ሲሆን ዘር ተኮር ግን አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አብን በመግለጫው መሳሪያ የታጠቁ ገዳዮችን በመደገፍና እንዳላዩ በማለፍ ለጥቃቱ መዋቅራዊ ከለላ የሰጡና በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የዘር ማጥፋቱ ተባባሪ የሆኑ የክልሉ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲል የጠየቀ ሲሆን ዋና አሰተዳዳሪው አቶ አትንኩት ግን የአመራር ክፍተት ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ይሁንና አሁን ላይ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ የሥራ ሃላፊዎችን የማጥራት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ከአል ዐይን ባደረጉት ቆይታ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጸመው ተራ ግጭት፣ሁከት አሊያ ግርግር ሳይሆን ብሔርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ነው ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን የሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ ግድያ ቢፈጸምም እነርሱ ግን የተገደሉት የድርጊቱ ተባባሪ ባለመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
በመተከል ዞን በተደጋጋሚ ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ አንዳንድ ቀበሌ አመራሮች መረጃው አስቀድሞ ደርሷቸው እንደነበር አንስተው ነገር ግን የራሳቸውን ቤተሰብ በማሸሽ ሌላው እንዲጎዳ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስም ቢሆን ቀድሞ መከላከል ነበረበት የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ተቀባነት የለውም ያሉት አቶ ግዛቸው የዚህ የመጀመሪያ ተጠያቂ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
በመተከል እየተፈጸመ ላለው ችግር ዘላቂው መፍትሄ ምንድነው?
በመተከል ዞን ከተካሄደው ጭፍጨፋ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ ኃይል በወሰዳቸው እርምጃ አብዛኞቹ መደምሰሳቸው ተገልጿል፡፡ በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩና የንጹሃንን ሕይወት ሲቀጥፉ የነበሩ ሽፍቶችም መገደላቸው ተነግሯል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የመሩት የፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በሥፍራው ተገኝቶ ውይይት ካደረገ በኋላ ዘላቂ ያለውን መፍትሄ ማስቀመጡን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው በተደጋጋሚ ግጭት እየተፈጸመ ስለሆነ አማራ በቀበሌ አደረጃጀት፤ በፖሊስ መዋቅር፤ በወረዳ፣ በዞን እና በክልል አመራር ላይ ያገለለ መሆኑ በግምገማ መነሳቱን አቶ ግዛቸው አንስተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚሊሻ ሲታጠቅ አማራ እና አገው እየተሳተፉ አለመሆኑንና አለመሳተፋቸው መረጃ እንዳይደርሳቸው መደረጉም የሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግስት አመራሮች ባሉበት በግምገማ መነሳቱን አቶ ግዛቸው አስታውቀዋል፡፡
አሁን የታጠቁ ሃይሎች መሳሪያቸውን እንዲያወርዱ እና አማራን ጨምሮ ሁሉንም ብሔሮች የሚወክሉ እና ብቃቱ ያላቸው በአደረጃጀት እንዲካተቱ እና እንዲታቀፉ ከዚያም ወደ ቀበሌ እና ወደ ወረዳ መዋቅር እንዲገቡ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ግዛቸው የፍትሕ አካላት በዚህ የተሳተፉትን በሙሉ ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ መግባባት ላይ መደረሱን የገለጹት አቶ ግዛቸው ፍርድ ቤቶችም በወንጀል የተሳተፉትን ፍርድ ከመስጠት አንጻር ችግር እንደነበረባቸው መገለጹን ነው ያነሱት፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተፈጸመውን ጭፍጨፋ እንዲመረምር፣ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፍርድ ሂደቱን የሚጣራ ግብረ ኃይል እንዲያቋቋም ተወስኗል ብለዋል፡፡
የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ ግድያ እየተፈጠረ መቀጠል የለበትም ያሉት አቶ ግዛቸው ከላይ ውሳኔ ላይ ያረፉ ጉዳዮች በሦስት ሳምንት ውስጥ ይገመገማሉ ብለዋል፡ አሁን ላይ በጭፍጨፋው የተሳተፉ ከ300 በላይ የጥፋት ኃይሎችና ግብረ አበሮቻቸው በሕግ ተይዘዋል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
አብን በሰሞኑ በተደረገው ጭፍጨፋ “ከ 160 በላይ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል” ሲል ገልጿል፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈፀመው ጥቃት ተራ የማሕበረሰቦች ግጭት ወይም የሽፍቶች ድርጊት ውጤት ሳይሆን በአማራ ጠል ትርክት ላይ የተመሰረተ፣ ስልታዊ የሆነ እና በመንግሥታዊ መዋቅር ጭምር የተደገፈ የሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን በመግለጫው ላይ አስፍሯል፡፡