31 ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች በመጀመሪያው በረራ ከዩኬ ወደ ረዋንዳ ሊሳፈሩ ነው ተባለ
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ፤ ውሳኔውን “በደስታ የተቀበልኩት ዜና ነው” ብለዋል
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡደኖች “በግዳጅ ሊባረሩ” የተዘጋጁት ሰዎች ደኅንነት ያሳስበናል እያሉ ነው
31 ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች በመጀመሪያው በረራ ከብሪታኒያ ወደ ረዋንዳ በመጪው ማክሰኞ ሊሳፈሩ ነው ተባለ፡፡
ሩዋንዳ፤ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል የሚልየን ዶላሮች ስምምነት ባለፈው ወር ከብሪታኒያ ጋር መፈራረሟ የሚታወስ ነው፡፡
በስምምነቱ መሰረት፤ ብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመመለሱ ተግባር ከመጪው ወርሃ ሰኔ 14 ቀን 2022 ጀምሮ ማከናወን እንደምትጀምር ማስታወቋም አይዘነጋም፡፡
ይህ አከራካሪ ሆኖ እየቀጠለ የመጣው ጉዳይ ‘የፈጣሪን ስራ የሚጻረር’ ተግባር መሆኑ ከሃይማኖት መሪዎች ጀምሮ እስከ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲተቹት የነበረ ጉዳይ መሆኑም የሚታወቅ ነው፡፡ በመጠለያዎች ውስጥ ከነበሩ ስደተኞች ጥቂት የማይባሉ እየጠፉ እንደሆነም ሲነገር ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ አወዛጋቢው የጥገኝት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ የመመለስ ጉዳይ፤ በመጨረሻም ቢሆን በብሪታኒያ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ይሁኝታ እንዳገኘ ተግልጿል፡፡በዚህም መሰረት “31 ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች በመጀመሪያው በረራ ከብሪታኒያ ወደ ረዋንዳ በመጪው ማክሰኞ ሊሳፈሩ ነው” መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጉዳዩን አጥብቀው ሲቃወሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡደኖች ሲያደርጉት ነበረ ጥረት ባይሳካላቸውም፤ “በግዳጅ ሊባረሩ” የተዘጋጁት ሰዎች ደኅንነት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል። ጉዳዩን ሰኞ ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱትም አረጋግጠዋል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከቀጣዩ ወር መጨረሻ በፊት ፖሊሲው ላይ የቀረበውን ተቃውሞ ያዳምጣል ተብለዋል።
ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ ስዊፍት፤ “ለህዝብ ጥቅም" ሲባል የሀገር ውስጥ ሚንስትር ፕሪቲ ፓቴል ፖሊሲዎችን መተግበር አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
ፓቴል ውሳኔውን በማድነቅ መንግስት ዕቅዶቹን መተገበር ይቀጥላል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ደግሞ ውሳኔውን “በደስታ የተቀበልኩት ዜና” ሲሉ ገልጸዋል ።
ብሪታኒያ በርካታ ስደተኞች ከሚያስተናግዱ አውሮፓ ሀገራት አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ ከ4 ሺ 850 በላይ ስደተኞች ወደ ብሪታኒያ የገቡ ሲሆን ቁጥሩ ባለፈው ዓመት ከነበረው 831 የስደተኞች ቁጥር በእጅጉ የላቀ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወደ ስልጣን ሲመጡ የህገ ወጥ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ቃል ቃል ገብተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም ቁጥሩ በገቡት ቃል ልክ ከመቀነስ ይልቅ ስለመጨመሩ ይነገራል፡፡
የሩዋንዳው ስምምነት ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ጫና ለመቅለል በማሰብ የተደረገ እንደሆነም ነው የሚነገረው፡፡በብሪታኒያ 44 ሺ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞቸ እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡