ዴንማርክ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመመለስ ከሩዋንዳ መንግስት ጋር ንግግር መጀመሯ አስታወቀች
ዴንማርክ ላለፉት በርካታ ዓመታት ስደተኞችን ለመከልከል የሚያስችሉ ጠንካራ ፖሊሲዎች ስታረቅ የነበረች ሀገር ናት
ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመመለሱ አቅድ ከ160 በላይ በሚሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ገጥሞታል
የዴንማርክ መንግስት እንደ ብሪታኒያ ሁሉ፤ በሀገሩ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች ጉዳይ በሩዋንዳ ለማየት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሩዋንዳ መንግስት ጋር ውይይት መጀመሩ አስታውቋል፡፡
የዴንማርክ መንግስት ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ስደተኞችን ለመከልከል የሚያስችሉ ጠንካራ ፖሊሲዎች ሲያረቅ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
በተለይም በባለፈው ዓመት፤ በሀገሪቱ ጥገኝነትን የሚጠይቁ ስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ፤ በሌሎች አጋር ሀገራት ሆነው የሚከታተሉበት የህግ አሰራር ማጸደቋ የሚታወስ ነው፡፡
በወቅቱ ዴንማርክ ያጸደቀቸው ህግ፤ በተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች ተቋማትና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞትም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ፤ በወቅቱ ጉዳዩን ለማሳለጥ አብረዋት የሚሰሩ ሀገራት እንዳላገኘች ገልጻ የነበረቸው ዴንማርክ፤ አሁን ላይ ከሩዋንዳ ጋር ንግግር ጀምሬያለው እያለች ነው፡፡
የሩዋንዳ መንግስት ከአሁን በፊትም ቢሆን በተመሳሳይ መልኩ ከእስራኤልና ሊቢያ ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች ሲቀበል መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በቅርቡም፤ የሩዋንዳ መንግስት በብሪታንያ የሚገኙ ስደተኞች ተቀብሎ ለማስተናገድና ጉዳያቸው በሩዋንዳ ሆነው እንዲያሳልጡ የሚያስችል የሚልዮን ዶላሮች ስምምነት ከብሪታንያ መንግስት ጋር ፈጽሟል፡፡
157 ሚሊየን ዶላር እንደሚሸፍን የተነገረለት ስምምነት፤ ህገወጥ ስደትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ላለችው ብሪታኒያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ነው የተገለጸው።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሴንት ቢሩታ "ስምምነቱ የስደተኞችን ደህንነት እና ክብር የሚያስጠብቅ እንዲሁም የመኖር ፍላጎት ካላቸው በቋሚነት እንዲሰፍሩ መብት የሚሰጥ ነው" ማለታቸው አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ፤ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመመለሱ እቅድ የበርካቶችን ነቀፌታ እያስተናገደ ይገኛል፡፡
እስካሁን ከ160 በላይ የሚሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች "ጨካኝ" ነው ያሉት እቅድ የተቃወሙ ሲሆን፤ የብሪታኒያ መንግስት እንዲሰርዘው ጠይቋል፡፡
የብሪታኒያ አንግሊካን ቤተ-ክርስትያን ሊቀ-ጳጳስ ጃስቲን ወልቢ የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ ፤እቅዱ "ትልቅ ሞራላዊ ጥያቄ" የሚያስነሳ ነው ብለውታል።
እርምጃው " በአምላክ ፊት ለፍርድ የሚያስቆም ነው" ሲሉም አውግዘውታል ጳጳሱ።
በርካታ ዜጎቿ ወደ አውሮፓ ምድር እንደሚሰደዱባት የሚገርላት ኤርትራም ብትሆን እቅዱን “አሳፋሪና ርካሽ” ነው ስትል ነቅፈዋለች፡፡
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፤ሩዋንዳ ለገንዘብ ስትል የእቅዱ አካል መሆኗ ልትወገዝ ይገባልም ብሏል።