በስዊዝ ቦይ መዘጋት ምክንያት መተላለፊያ አጥተው የቆሙ መርከቦች ቁጥር ከ320 አለፈ
መተላለፊያ አጥተው ከቆሙት መርከቦች መካከል የኢትዮጵያ መርከቦች እንደሚገኙበት ተገልጿል
ስዊዝ ቦይን የዘጋው ‘ኤቨር ጊቭን’ መርከብ ለሳምንታት እዛው ሊቆይ ይችላል
በዓለም ላይ እጅግ ከተጨናነቁ የንግድ መርከብ መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው የግብፁ ስዊዝ ቦይ መተላለፊያ ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ በታይዋን ኩባንያ ‘ኤቨርግሪን ማሪን’ በሚተዳደረው ‘ኤቨር ጊቭን’ በተሰኘ መርከብ መዘጋቱ ይታወሳል።
መርከቡ ከቀይ ባህር ወደ ሜዲተራኒያን ባህር በሚሻገርበት ወቅት በከፍተኛ ንፋስ በድንገት በመመታት በቦዩ መተላለፊያ ላይ በጎኑ ተዘርግቶ በመቆም ነው ቦዩ እንዲዘጋ ያደረገው፡፡
በስዊዝ ቦይ መዘጋት ምክንያት ከቀይ ባህር ወደ ሜዲተራኒያን ባህር እንዲሁም ከሜድትራኒያን ወደ ቀይ ባህር ለመሻገር በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ መርከቦች ቁጥር 321 መድረሱን የሲ.ጂ.ቲ.ኤን. ዘገባ ያመለክታል።
በስዊዝ ቦይ ላይ መተላለፊያ አጥተው ከቆሙት መርከቦች መካከል የኢትዮጵያ መርከቦች እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለኢቢሲ አስታውቋል።
የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ የስዊዝ ቦይ መዘጋት በኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ላይ ተፅእኖ እንዳለው ተናግረዋል።
እስከ ባለፈው እለተ አርብ ድረስ ብቻ ከሞሮኮ ማዳበሪያ በመጫን ወደ ጅቡቲ በመጓዝ ላይ የነበረ፣ ማዳበሪያ ለመጫን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሞሮኮ በመጓዝ ላይ የነበረ እንዲሁም ከጥቁር ባህር ወደ ቀይ ባሕር ለመሻገር በመጓዝ ላይ የነበረ አሶሳ የተባለ ግዙፍ መርከብ እና ሌሎችም በኮንትራት ለኢትዮጰያ እቃ የሚጓጉዙ መርከቦች መተላፊያ አጥተው መቆማቸውን አሰታውቀዋል።
የግብፅ ስዊዝ ካናል ባላስልጣን በበኩሉ መንገድ ተዘግቶባቸው የቆሙ መርከቦች ቁጥር 321 መድረሱን እና በመጠባበቅ ላይ ላሉ መረከቦች አስፈላጊው የሎጅስቲክስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ ዋስ ስራ አስፈጻሚ ኦስማን ራቢ መርከቡ መቼ ይነሳል የሚለውን ትክክለኛ ጊዜ ለመናገር ከባድ መሆኑን ተናረዋል።
በአሁኑ ወቅትም 14 ጎታች መርከቦች ‘ኤቨር ጊቭን’ መርከብን ለማንቀሳቀስ እየሰሩ መሆኑን እና ትናንት ምሽት ተስፋ ሰጪ ምልክት መታየቱንም ተናግረዋል።
የስዊዝ ቦይን የዘጋው ‘ኤቨር ጊቭን’ የተሰኘ መርከብ የ224 ሺ ቶን ክብደት ፣ 400 ሜትር ርዝመት እና 59 ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡
የስዊዝ ቦይ ሜዲተራኒያን ባህርን ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኝ መተላለፊያ መስመር ሲሆን፤ እሲያ እና አውሮፓ በአቋራጭ የሚገናኙበት መስመርም ነው።
የዓለማችን 12 በመቶ የሚሆነው የንግድ መርከብ በዚሁ በስዊዝ ቦይ በኩል እንደሚተላለፍም መረጃዎች ይጠቁማሉ።