ኮንቴይነሮችን በጫነች ግዙፍ መርከብ የተዘጋው ስዊዝ ቦይ እስካሁን አልተከፈተም
‘ኤቨር ግሪን’ን እስከ ዛሬ (ቅዳሜ) ማታ ድረስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል
መተላለፊያ ቦዩ ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ ነው የተዘጋው
ኮንቴይነሮችን በጫነችና ‘ኤቨር ግሪን’ በተባለች ግዙፍ መርከብ የተዘጋው የግብጽ ሰዊዝ ቦይ መተላለፊያ የባህር ላይ መንገድ እስካሁን አልተከፈተም፡፡
መተላለፊያው ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ ነው የተዘጋው፡፡
በዚህም ለወትሮው በሰው ሰራሽ ባህሩ ላይ እንደልብ ይተላለፉ የነበሩ የንግድ መርከቦች ዛሬን ጨምሮ ከሰሞኑ ለመተላለፍ አልቻሉም ተብሏል፡፡
መተላለፊያውን ለመክፈት ትናንት ጭምር የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ሮይተርስ የአካባቢውን ምንጮች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡ ሮይተርስ ጥረቱ ዛሬም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የዘገበው፡፡
መተላለፊያውን የሚያስተዳድረው ባለስልጣን መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ኦሳማ ራቢ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫን እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡
የ‘ኤቨር ግሪን’ ባለቤትነት የታይዋን ባለሃብቶች ነው፡፡ ሆኖም ‘ሾይ ኪሰን’ የተባለ የጃፓን የሎጂስቲክ ተቋም ነው በኪራይ ይጠቀምባት የነበረው፡፡
የተቋሙ ኃላፊዎች ትናንት በሁለተኛዋ ግዙፍ የጃፓን ከተማ ኢማባሪ በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከመቀመጫቸው ተነስተው አጎንብሰው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
‘ኤቨር ግሪን’ን እስከ ዛሬ (ቅዳሜ) ማታ ድረስ ዘግታ ከቆመችበት የመተላለፊያው ስፍራ ለማንቀሳቀስ እንደሚሰሩም ነው ያስታወቁት፡፡
ምክንያቱ እየተጣራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ስዊዝ ቢያንስ በቀን 10 ቢሊዬን ዶላር ዋጋ ያላቸው የንግድ ቁሳቁሶች የሚጓጓዙበት ነው፡፡
‘ኤቨር ግሪን’ ብቻዋን የ1 ቢሊዬን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ቁሳቁሶች የያዙ ኮንቴይነሮችን እንደጫነች ተነግሯል፡፡
መተላለፊያው ስራ ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ1869 ጀምሮ እንዲህ ስራ አቁሞ ተዘግቶ የቆየው ለሁለት አጭር ጊዜያት ብቻ ነው፡፡
አንደኛው የወቅቱ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጋማል አብደል ናስር የስዊዝን የባለቤትነት መብት ግብጽ ጠቅልላ እንድትይዝ ባደረጉበት ጊዜ (በ1957/58) ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በሁለቱ የአረብ-እስራኤል ጦርነቶች ወቅት ያጋጠመ ነበር፡፡