የስዊዝ ቦይ በመርከብ በመዘጋቱ ምክንያት በየቀኑ የ9 ቢሊየን ዶላር ንግድ እያተስተጓጎለ መሆኑ ተገለፀ
በስዊዝ ቦይ መዘጋት ተነሳ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል
ኤቨርግሪን መርከብ ለሳምንታት በስዊዝ ቦይ ሊቆይ ይችላል
የስዊዝ ቦይ በኤቨርግሪን መርከብ በመዘጋቱ ምክንያት በየቀኑ የ9 ቢሊየን ዶላር ንግድ እየተስተጓጎለ መሆኑ ተገለፀ
በዓለም ላይ እጅግ ከተጨናነቁ የንግድ መርከብ መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው የግብፁ ስዊዝ ቦይ መተላለፊያ ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ የ224 ሺ ቶን ክብደት ፣ 400 ሜትር ርዝመት እና 59 ሜትር ስፋት ያለው ‘ኤቨር ግሪን’ የተሰኘ መርከብ መዘጋቱ ይታወሳል።
መርከቡ ከቀይ ባህር ወደ ሜዲተራኒያን ባህር በሚሻገርበት ወቅት በከፍተኛ ንፋስ በድንገት በመመታት በቦዩ መተላለፊያ ላይ በጎኑ ተዘርግቶ በመቆም ቦዩ እንዲዘጋ ማድረጉም ታውቋል።
በስዊዝ ቦይ መዘጋት ምክንያት 150 መርከቦች ከቀይ ባህር ወደ ሜዲተራኒያን ባህር ለመሻገር በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የሲ.ጂ.ቲ.ኤን. ዘገባ ያመለክታል።
የስዊዝ ቦይ መዘጋት የዓለም ንግድን በእጅጉ እያስተጓጎለ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ በዚህም 9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ንግድ በየእለቱ እየተስተጓጎለ መሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በስዊዝ ቦይ መዘጋት የተነሳ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል ፤ በመተላለፊያ መስመሩ መዘጋት ሰበብ የድፍድፍ ነዳጅ አቅርቦት ሊስተጓጎል ይችላል በሚል ስጋት በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱም ተነግሯል።
ጃፓናዊው የኤቨርግሪን መርከብ ባለቤት መርከቡ የስዊዝ ቦይን በመዝጋቱ የዓለም ንግድ ላይ ለፈጠረው መስተጓጎል ይቅርታ ጠይቀዋል።
የስዊዝ ቦይ ባለስልጣን መርከቡን ከስፍራው ለማንሳት እየሰራ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ እስካሁን በተሰራው ስራም መጠነኛ ለውጥ መታየቱ ተነግሯል።
ከጃፓን እና ከኔዘርላንድስ የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም መርከቡን በፍጥነት ለማንሳት ከግብፅ ባለስልጣናት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸው ተሰምቷል።
ሆኖም ግን ኤቨርግሪን ለሳምንታት በስዊዝ ቦይ ሊቆይ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለም ነው የተገለጸው።
ስዊዝ ቦይ የዓለማችን 10 በመቶ የሚሆነው የንግድ መርከብ የሚመላለስበት ፣ ሜዲተራኒያን ባህርን ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኝ መተላለፊያ መስመር ነው፡፡ ይህ ቦይ እሲያ እና አውሮፓ በአቋራጭ የሚገናኙበት መስመርም ነው።