በለይቶ ማቆያው እስካሁን 506 ኢትዮጵያውያን ነበሩ
ደወሌ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ 325 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ከማዕከሉ ይወጣሉ
ሱማሌ ክልል ሽንሌ ዞን ደወሌ ከተማ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ከነበሩ 506 ሰዎች 325ቱ ዛሬ ማዕከሉን ለቀው እንደሚወጡ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዩሱፍ መሃመድ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ሰዎቹ ማዕከሉን ለቀው የሚወጡት የነበራቸውን የ14 ቀናት የቆይታ ጊዜ በማጠናቀቃቸውና ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ነው፡፡
“ሁሉም ከጅቡቲና ከአጎራባች የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች የመጡ ኢትዮጵያውን ናቸው” ያሉት ቢሮ ኃላፊው ወደየአካባቢያቸው የሚያደርሳቸው የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡
ድንበር እያቋረጡ ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ከጅቡቲ፣ከሶማሊያ ከኬንያም ነው የሚመጡት፤ ትናንት ብቻ 110 ዜጎች መጥተዋል” ሲሉ መልሰውልናል፡፡
በሶማሌ ክልል እስካሁን ከፑንትላንድ መጣ የተባለ 1 ሰው በቫይረሱ መያዙ ሪፖርት ተደርጓል፡፡
የማዕከሉ መኖር በድሬዳዋ እና አካባቢው ላይ ሊደርስ የሚችለውን የወረርሽኙ ጫና የሚያቀል ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ ስለ ጉዳዩ የጠየቃቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ከአሁን ቀደም “ከአሁን ቀደም በጅቡቲ ድንበር በኩል ጥብቅ ቁጥጥር አልነበረንም፤በዛ ምክንያት መጀመሪያ አካባቢ የተወሰኑ ሰዎችን ተቀብለናል” ብለዋል ደወሌ ላይ እንዲቆዩ መደረጉ ጫናውን እንዳቀለለው በመጠቆም፡፡
“በህገወጥ መንገድ የሚገቡትን ና ሰፈር ውስጥ ያሉትን ጭምር ለቢሮው በሚደርሱ ጥቆማዎች ተለይተው እንዲቆዩ ይደረጋል” ሲደረግ እንደነበርም ነው ወ/ሮ ለምለም የገለጹት፡፡
ከጅቡቲ መጥተው ድሬዳዋ ወደሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች የገቡ 700 ገደማ ሰዎች እንዳሉ ለአል ዐይን የደረሱ የአስተዳደሩ ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በድሬዳዋ በአሁኑ ሰዓት (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) 6 ከጅቡቲ የመጡ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ለይቶ ማቆያ ይገኛሉ፡፡
ከአሁን ቀደም ከአውስትራሊያ መጥቷል የተባለውን ግለሰብ ጨምሮ ከእሱ ጋር ግንኙነት የነበራት የአስተዳደሩ ነዋሪ ከቫይረሱ አገግመው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል መባሉም የሚታወስ ነው፡፡