አንዴ ተዘርቶ ለረዥም ዓመታት የሚቆይና ተደጋጋሚ ምርትን ነው የሚሰጥ የተባለለት የምርምር ስራው በድጋፍ እጦት ምክንያት ነው ሊኮበልል የተቃረበው
ሊኮበልል የተቃረበው ሃገር በቀል የምርምር ስራ
ስለዚህ የምርምር ስራ ብዙ ብዙ ተብሏል፡፡ አዲስ የፈጠራ ሃሳብ ስለመሆኑም ዋና ዋና በሚባሉ የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ጭምር ተነግሮለታል፡፡ በሳይንስና ምርምር ዘርፍ ያሉ እና የነበሩ አመራሮችም አዲስ ግኝት ስለሆኑ መስክረውለታል፡፡ የያኔው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአሁኑ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ግሩም ሲል ግኝቱን አድንቆ የገንዘብ ድጋፍን አድርጎለታል፡፡ በአቶ ታለጌታ ልዑል እና በተመራማሪ ባልደረቦቻቸው ለተገኘውና አንዴ ተዘርቶ ከ5 እስከ 7 ለሚደርሱ ዓመታት ምርትን መስጠት እንደሚችል ለተነገረለት የማሽላ ምርጥ ዘር፡፡
በምርምር ስራው “የማያጠራጥር ጥሩ ውጤት አግኝተናል” የሚሉት ዋና ተመራማሪው አቶ ታለጌታ “መረጃዎችን በመሰብሰብና በማጥናት ሰብሉ [ማሽላው] ሊበቅል እንደማይችል በሚታሰብባቸው የስነ ምህዳር ይዞታዎች ላይ ጭምር በቆላ፣በደጋና በወይና ደጋ አካባቢዎች እንደሚበቅል አረጋግጠናል” ይላሉ፡፡
የብዙዎችን አድናቆት ያገኘው የምርምር ስራው በዓመት ከ2 እስከ 3 ጊዜ ምርት የሚሰጥ ነው፡፡ እንደ መሬቱ የአፈር ይዞታና እንደ አካባቢው ስነ ምህዳር ቢሊያይም በተዘራበት የመጀመሪያ ወቅት በሄክታር 60 ኩንታል፣በ2ኛው ዙር 75 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥና በቀጣዮቹም ዙሮች እንደዚሁ የተሻለ ምርት እንደሚገኝበት ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
እንደተመራማሪው ገለጻ ዝርያው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በእንስሳት መኖነትም ሊውል የሚችል ነው፡፡ በደረቃማ የበጋ ወራት ሁሉ ልምላሜ ያለው መሆኑም ለእንስሳት እርባታና ማድለብ ተግባርም ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
ይህንኑ “የምርምሩን ውጤታማነት በሰርቶ ማሳያ ቦታችን ጭምር ተገኝቶ በመመልከትና በማረጋገጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ2 ነጥብ 8 ሚሊዬን ብር ድጋፍ አድርጎልን ነበር” የሚሉት ዋና ተመራማሪው ለስራቸው የሚሆን ማረጋገጫን ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለማግኘት ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት አለመሳካቱ ከሚኒስቴሩ ጋር አብሮ ለመስራትም ሆነ ስራቸውን ይበልጥ ለማስፋት እንዳላስቻላቸው ይናገራሉ፡፡
“እንዲያውም በኢንስቲትዩቱ በኩል ያለው ነገር ተስፋ አስቆራጭ ነው“ ሲሉም ነው የሚያስቀምጡት፡፡ ለምን እንዲያ ሊሆን እንደቻለ ሲጠየቁም፡
“የምርምር ስራውን ለማረጋገጥ ጥርጣሬ አድሮባቸዋል፤በተዓምር ምርት የሚሰጥ አይደለም በየትኛውም ዓለምም አልተሰራም ‘ገቦ’ [ምርት የማይሰጥ] ነው በሚል ስራችንን ለማጣጣል እየሞከሩ ነው” ሲሉ በምሬት ይናገራሉ፡፡
ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነና የተሻለ ምርት መስጠት እንደሚችል በተጨባጭ ደጋግመንም አሳይተናል የሚሉም ሲሆን ከቲዮሪ እና ከላቦራቶሪ ወጥቶ ከፍተኛ ምርት መስጠት እንደሚችል በሚቀርቡን ገበሬዎች በኩል በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሞክረው ስለማሳየታቸው ይናገራሉ፡፡
“እነሱ ሊሰሩት ይገባ የነበረውን ነገር ሰርተን በማሳየታችን እና ስራው በእነሱ በኩል ባለማለፉ ምክንያት ሊደግፉን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል”ም ይላሉ፤ምርምሩ ችግሮች ቢኖሩበት እንኳን እያሟሉ እና የምርት መጠኑን እያሳደጉ የንጥረ ምግብ ይዞታውንም ከፍ እያደረጉ መጠቀም እንደሚገባ በመጠቆም፡፡
የምርምር ስራውን ለማረጋገጥ በተቋሙ የተጠየቁት ክፍያም አንዱ የተመራማሪዎቹ የቅሬታ ምንጭ ነው፡፡ ለአንድ ዓመት 250 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ስለመጠየቃቸውም አልሸሸጉም፡፡
“ይህ የቀን ስራ እየሰራሁ እዚህ ላደረስኩት ሰው እንዴት ይቻለኛል፤አቅሜም አይፈቅድም 4ቱን የምርምር ስራዎች ለማረጋገጥም እስከ አንድ ሚሊዬን ሊደርስ የሚችል ክፍያን የሚጠይቅ ነው እስከ 4 ዓመት ከዚያም በላይ ምርት የሚሰጥ መሆኑ ደግሞ በትንሹ በ4 አመት እንኳን ቢታሰብ 4 ሚሊዬን ብር ይጠይቀኛል” ሲሉም ነው ክፍያው ነገር ከአቅማቸው በላይ መሆኑን የሚያስቀምጡት፡፡
ምርምርን በተመለከተ ሃገሪቱ ያወጣችው ህግም የሚያበረታታ አይደለም ሲሉም ይተቻሉ፡፡
አል ዐይን አማርኛም በተመራማሪው የተነሳውን የቅሬታ ሃሳብ ይዞ “ማረጋገጫ ሊሰጠኝ አልፈለገም” በሚል የወቀሱትን ተቋም ጠይቋል፡፡ የኢንስቲትዩቱን የሰብል ምርምር ዘርፍ ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ታደሰንም አነጋግሯል፡፡
ሆኖም ዳይሬክተሩ “ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለምርምሩ እውቅና ቢሰጥም እና ግብርናና ገጠር ልማት ቢያረጋግጠውም ሳይንሳዊ የሆነና የተጨበጠ ነገር አላገኘንበትም” ብለዋል፡፡
የምርምር ስራውን ሳያረጋግጡ “የተጨበጠ ነገር አላገኘንበትም” ስለማለቱ ተገቢነት ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ለማረጋገጥ ብዙ ጊዜ ጠይቀናል፤መረጃዎች ተሰብስበው መተንተንና ሳይንሱ በሚፈቅደው ልክ መሰራት ነበረባቸው” ይላሉ፡፡ ስለ ሁኔታው ዘርዘር አድርገው ሲያስረዱም
“እኛ ስራውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ የሚያስችል የቴክኒክ ድጋፍን እንድናደርግላቸው፤ እነሱ ፋይናንስ እንዲያደርጉ ጠይቀናል፤ይህን ማድረግ ግን አልቻሉም ተቋማችን ደግሞ በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደር ተቋም ነው፤ባለቤትነቱ የግለሰብ የሆነን ስራም ከህግ ውጪ ያለ ክፍያ ማረጋገጥ አንችልም” በሚል ያስቀምጣሉ፡፡
ከዚህ ውጪ ሊያስኬድ የሚችል ሌላ ሁለተኛ አማራጭም እንዳለ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ “ቴክኖሎጂውን በውለታ ሰጥተውን እኛ ልናረጋግጥና ወደ ተጠቃሚው ልናደርስ የምንችልበት አጋጣሚምም አለ” ይላሉ እንደ አማራጭ ሊወሰድ ይችል እንደነበር በመጠቆም፡፡ ሆኖም ስራው በጋራ መስራት፣መረጃውንና ዘሩን ማቅረብ የሚጠይቅ በመሆኑ ሰዎቹ ለዚህ ፍቃደኛ አይደሉም እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
“ምርምሩን በራሳቸው ማሳ ነው የሚያካሂዱት ማሽላ የሚበቅለው የት ነው በአዲስ አበባ አይበቅልም በአብቃይ አካባቢዎች ብቻ ነው በራሳቸው ማሳ ውጤታማነቱን ማረጋገጥ አንችልም” ሲሉም ያክላሉ፡፡
የተቋሙ አመራር (ማኔጅመንት) ካልፈቀደ በስተቀር ያለ ክፍያ ሊሰሩ እንደማይችሉም ነው ዳይሬክተሩ የሚናገሩት፡፡
የዳይሬክተሩን ምላሽ በመያዝ ቀጣይ ያሰቡት ነገር እንዳለ የጠየቅናቸው ተመራማሪው አቶ ታለ ጌታም
“ከኬንያ እና ከአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ተመራማሪዎች ጋር ተነጋግሬ በስራው ተደስተዋል አስፈላጊውን ከፍያ ለመፈጸምም ተስማምተዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡መነጋገራቸው ምን ለማድረግ እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄም
“ሃገሬ ካልፈለገችው ለሚፈልጉት ሸጬ ራሴን ለማኖር እገደዳለሁ” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ሃገር በቀል የምርምር ስራዎች እንዲበራከቱ በማሰብ ብቻም ሳይሆን ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ በሚሰራበት በዚህ ወቅት ስለ ምርምር ስራው መኮብለል የጠየቅናቸው ዶ/ር ታዬ፡
“ይደግፈናል ብለው ወደሚያስቡት ወዴትኛውም ሃገር ቢወስዱት አይከፋንም” ሲሉ መልሰውልናል፡፡
[ ማስታወሻ፦ይህ ዘገባ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት የተዘጋጀ ነው፡፡ ሰዎቹም በወቅቱ የተጠየቁ ናቸው፡፡ጉዳዩን የተመለከተ አዲስ ለውጥ እንደሌለም ተመራማሪው ገልጸውልናል፡፡]