ኮሮና እና የግሉ ዘርፍ ድርሻ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ አባላት ከግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ጋር ተወያይተዋል
የአፍሪካ መሪዎች የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከሉ ሂደት የግሉ ዘርፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጠየቁ
የአፍሪካ መሪዎች የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከሉ ሂደት የግሉ ዘርፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጠየቁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በተመራው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ አባላት የቪዲዮ ዉይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ውይይቱ በዋናነት ወርርሽኙን በመዋጋቱ ሂደት ህብረቱ በጀመራቸው የቤት ስራዎች የግሉ ዘርፍ ምን ድርሻ ሊኖረውና ምን ዓይነት ሚናን ሊጫወት እንደሚችል መምከር ላይ የሚያተኩር ነበረ፡፡
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣የኬንያ፣የማሊ፣የርዋንዳ፣የሴኔጋል፣የዚምባብዌ መሪዎችን ጨምሮ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ እና የአፍሪካ የንግድ ሰዎች ጥምረት (African Business Leaders Coalition) አባላት በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ ከ20 የሚበልጡ አፍሪካውያን የንግድ ሰዎች መሳተፋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል” ብለዋል፡፡
“የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአፍሪካ የወጪ እና የገቢ ንግድ ባንክ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለአፍሪካ ኮቪድ ፈንድ፣ ለአፍሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል ድጋፍ ለማድረግ ያላቸው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ” ስለመሆኑም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስማቸው ባለው ይፋዊ የማህበረሰብ ትስስር ገጽ ያሰፈሩት፡፡
“እንደ አህጉር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከሉን ማጠናክር እንዲሁም ቫይረሱን የመመርመር አቅማችንን ማጎልበት በእጅጉ” እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪም የመመርመር አቅምን ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የግሉ ዘርፍ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
በግሉ ዘርፍ ያሉ ግብዓቶችን፣የግል ላቦራቶሪዎችን እና የማምረት ዐቅምን እንዴት አስተባብሮ በተጀመረው አህጉራዊ ጥረት መጠቀም እንደሚቻል መወያየታቸውንም ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ እንዴት ባለ መልኩ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ልምድና ተሞክሮ የሚያጋራና የሚለዋወጥበትን መድረክ እንደሚፈጥርም ህብረቱ አስታውቋል፡፡