በአደጋው የአራት ሰዎች ህይወት አልፏል
ከሟቾቹ መካከል አንዷ የ2 ወር ጨቅላ ናት
ትናንት ሚያዚያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ለ1 ሰዓት ያለማቋረጥ ሲጥል የነበረው ዝናብ ድሬዳዋን ዳግም ለጎርፍ አደጋ አጋልጧታል፡፡
አብዛኞቹን የከተማዋን ክፍሎች ያዳረሰው አደጋው በዋናነት 05፣04 እና 02 እንዲሁም 06 በተባሉ ቀበሌዎች ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን 05 ገንዳ አዳ በተሰኘ ቦታ አንድ ቤት ተደርምሶ አንድ የ2 ወር ጨቅላ እና የ4 ዓመት ህጻን ህይወታቸው አልፏል፡፡
ዝናቡን ተከትሎ በተፈጠረው ጎርፍ የተወሰዱ አንድ የ45 አመት ጎልማሳ እና የ19 ዓመት ወጣት ሃምዳይል ተብሎ በሚጠራ ቦታ አስከሬናቸው መገኘቱንምና በ2 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የአስተዳደሩ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ቀላል የማይባል ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ባደረሰው አደጋ ምክንያት ከ31 በላይ ቤቶች የፈረሱ ሲሆን በጎርፉ የተወሰዱ 3 የባጃጅና የፎርስ ተሽከርካሪዎች አሸዋ ዉስጥ ተቀብረዉ ተገኝተዋል፡፡
በርካታ የኤሌትሪክ ምሰሶዎች ወድቀዋል፣የመኖሪያና የመስሪያ ቤት አጥሮች ፈርሰዋል የተለያዩ የመደብር እቃዎች ስለመወሰዳቸውም ነው ለአል አይን አማርኛ የደረሱ መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡
የአስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ቢሮ የጉዳቱን መጠንና የተጎጂዎችን ሁኔታ የመለየት ተግባር በመከናወን ላይ ነው ብሏል፡፡
የአስተዳደሩ የመንገዶች ባለስልጣንም ተመሳሳይ ተጨማሪ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ የመፋሰሻ ቦዮችን እና መንገዶችን የማጽዳትእንዲሁም በ05፣08 እና 04 አካባቢዎች ደለል የመጥረግ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው፡፡
ከአደጋ ስጋት አመራር፣ከከንቲባ እና ከኮሙኒኬሽን ቢሮዎች የተውጣጣ ቡድን ጉዳት የደረሰበትን አካባቢ እና ተጎጂዎችን ጎብኝቷል፡፡
የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ላጡ እና ጉዳት ለደረሰባቸው በአደጋ ስራ አመራር በኩል ምግብና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ እንደሆነም ነው ኮሙኒኬሽን ቢሮው የገለጸው፡፡
የፈራረሱ ቤቶች ተመልሰው እንዲጠገኑ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮም ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች ከምግብና ከንጽህና ጋር የተያያዙ የወረርሽኝ መከላከል ህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት የተሟላ ዝግጅት እንዳለውም ገልጿል፡፡
በቀጣይም መስል ድንገተኛ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የአየር ትንበያዎች መረጃዎች አሳይተዋል ያለው የአስተዳደሩ ፖሊስ አሁን ህዝቡ ጥንቃቄን ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ድሬዳዋ ከዛሬ 14 ዓመታት በፊት በ1998 ዓ/ም ወርሃ ሃምሌ ላይ መጨረሻ ባጋጠማት ከባድ የጎርፍ አደጋ ከ250 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡