የስምምነቱ ፈራሚ አካላት በቀሪ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ተጠየቀ
የስምምነቱ ፈራሚ አካላት በቀሪ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ተጠየቀ
በዛሬው 71ኛው የኢጋድ አስቸኳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቪዲዮ ስብሰባ የተሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ፈራሚ አካላት በቀሩ ስራዎች ላይ ትኩረት እዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ፈራሚ አካላቱ የደረሱትን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ያሳዩትን ቁርጠኝነት ያደነቁት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለደቡብ ሱዳን ህዝብ እና ለቀጠናው መልካም ዜና ነው ብለዋል፡፡
የአንድነት የሽግግር መንግስት ለመመስረት በየካቲት 2012 ዓ/ም ስምምነት ላይ የደረሱት ፈራሚ አካላቱ እስከ ዛሬ ድረስ ያስመዘገቡትን አዎንታዊ ለውጥ ይበልጥ በማጠናከር በቀሪ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ስለማሳሰባቸውም ነው የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያስታወቀው፡፡
ስምምነቱ ከተደረሰ ወዲህ በርካታ አዎንታዊ ለውጦች መታየታቸውን በመጥቀስ በስምምነቱ የተሳተፉ ወገኖችን አመስግነዋል።
በተመሰረተው የአንድነት የሽግግር መንግስት ላይ ሚኒስትሮች እና ምክትል ሚኒስትሮች በሚያዟቸው ቦታዎች ላይ ስምምነት መድረሳቸውም ቀጣይ ስራዎችን ለማከናወን ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑም ነው አቶ ገዱ ያነሱት፡፡
በቀጣይ የክልሎች እና የአካባቢ መንግስታት የስልጣን ወሰን ላይ ስምምነት መድረስ በአገሪቱ አጠቃላይ ሰላምን በማስፈን በአሁኑ ስዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን የህግ አውጭውን አካል ማቋቋም፣ ሰላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ማስፈን እንዲሁም የደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ መደገፍ ላይ የኢጋድ አባል አገራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡትም ጠይቀዋል፡፡