በአሜሪካ አውሎንፋስ ከ30 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ
በርካታ ቤቶች እና ተሽከርካሪዎችን ያወደመው አውሎ ንፋስ በሰባት ግዛቶች ከ250 ሺህ በላይ ቤቶችን የኤሌክትሪክ ሃይል አቋርጧል

ኦክላሆማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሰደድ እሳቶችን እያቀጣጠለ መሆኑም ተገልጿል
በአሜሪካ ከባድ አውሎ ንፋስ በጥቂቱ የ34 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ተነግሯል።
በሚዙሪ ግዛት ብቻ የ12 ሰዎችን ህይወት የቀማው አውሎንፋስ በርካታ ተሽከርካሪዎችን እያላተመ አጋጭቷል፤ ቤቶችንም ወደ ፍርስራሽነት ቀይሯል።
በካንሳስ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ ከ55 በላይ ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው እንዲገለበጡ አድርጓል።
ሚቺጋን፣ ሚዙሪ እና ኢሊኖይስን ጨምሮ በሰባት ግዛቶች ከ250 ሺህ በላይ ቤቶች የኤሌክትሪክ ሃይል በአውሎ ንፋሱ ምክንያት መቋረጡን ፖወርአውቴጅ የተሰኘው ድረገጽ አስነብቧል።
ምስራቃዊ ሉዚያና፣ ምዕራባዊ ጎርጂያ፣ ማዕከላዊ ቴነሲ እና ምዕራባዊ ፍሎሪዳ በአውሎንፋሱ ከባድ አደጋ ይገጥማቸዋል ተብሎ ተተንብዩዋል።
የአሜሪካ ብሄራዊ የአየርንብረት አገልግሎት አውሎ ንፋሱን ተከትሎ የሚከሰተው ፈጣን ጎርፍ የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በቴኔሲ እኛ ሸልቢ የተመዘገበው አውሎ ንፋስ በስአት 97 ኪሎሜትሮች የሚጓዝ እንደነበር የሜትሮሎጂ ተቋሙ ይፋ ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሚዙሪ ግዛት 25 ክፍለግዛቶች 19 አደገኛ አውሎ ንፋስ መመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን፥ 12 ሰዎች የሚኖሩበት ቤት ወደፍርስራሽነት ተለውጦ ሁሉም ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።
አሊሽያ ዊልሰን የተባለው ከቤቷ በመውጣት ከአደጋው የተፈረች እንስት "በህይወቴ እንዲህ አይነት አስፈሪ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም፤ በጣም ፈጣን ነው፤ የጆሯችን ታምቡር ሊበጠስ ተቃርቦ ነበር" ብላለች።
በአውሎ ንፋሱ ሶስት ነዋሪዎቿ የሞቱባትና 29 የቆሰሉባት አርካንሳስ እና ጆርጂያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው አደጋው በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰሩ ነው።
ከሰባት በላይ ግዛቶችን ያዳረሰው አውሎ ንፋስ ኦክላሆማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ከ100 በላይ ሰደድ እሳቶች እያቀጣጠለ መሆኑም ተገልጿል።
በኦክላሆማ "840 ሮድ" የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሰደድ እሳት ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ አውድሞም ሊጠፋ አልቻለም።
በአሜሪካ ባለፈው አመት ከአውሎ ንፋስ ጋር በተያያዙ አደጋዎች የ54 ሰዎች ህይወት ማለፉ የተነገረ ሲሆን፥ ከላይ የተጠቀሱት ግዛቶች አደጋው ይደጋገምባቸዋል ተብሏል።