
ሞሮኮ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በድርቅ ተመታለች
ሞሮኮ ዜጎቿ በግ እንዳያርዱ አገደች፡፡
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ለሰባተኛ ተከታታይ ዓመታት በድርቅ የተመታች ሲሆን ይህን ተከትሎ ሀገሪቱ ካሏት እንስሳት ውስጥ 38 በመቶ ያህሉን አጥታለች፡፡
የሀገሪቱ ንጉስ አራተኛ ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዜጎች በግ ከማረድ እንዲቆጠቡ ትዕዛዝ አስተላፈዋል፡፡
በሞሮኮ ከሁለቱ የእስልምና ዕምነት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የኢድ አል አድሃ በዓል የዕምነቱ ተከታዮች በዓሉን በግ በማረድ በስፋት ያከብሩታል፡፡
ይህን ተከትሎ የፊታችን ሰኔ ወር ላይ በሚከበረው የኢድ አል አድሃ በዓል ላይ አማኞች በግ ከማረድ እንዲቆጠቡ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ድርቁን ተከትሎ በሞሮኮ የስጋ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ከውጭ ሀገራ ተገዝተው ለሚገቡ የስጋ እና ተያያዥ ምርቶች ላይ የተጣለው ቀረጥ እንዲነሳም ተደርጓል፡፡
ገበያውን ለማረጋጋት ሲባልም 100 ሺህ በጎችን ከአውስትራሊያ ያስገባችው ሞሮኮ ዜጎቿም የስጋ አጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ሞሮኮ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የምታገኘው ዓመታዊ ዝናብ መጠን በ53 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን ላለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታትም ድርቅ አጋጥሟል፡፡
አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ንጉስ መሀመድ አራተኛ አባት ሀሰን ሶስተኛ በፈረንጆቹ 1966 ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ሲያጋጥም ዜጎች በግ ከማረድ እንዲቆጠቡ ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላለፈው ነበር፡፡
ሀገሪቱ አሁን ያጋጠማትን ድርቅ ጉዳት ለመከላከል ውሃ በኮታ በማከፋፈል ላይ ስትሆን የግብርና ስራዎች ደግሞ ክፉኛ ከተጎዱ የስራ ዘርፎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡